ሳላዲን ሰዒድ ወደ ሜዳ ለመመለስ ተቃርቧል

ለረጅም ወራት ከሜዳ ርቆ የነበረው የፊት አጥቂ ዳግም የሚመለስበት ጊዜ ተቃርቧል።

የፈረሰኞቹ የፊት አጥቂ ሳላዲን ሰዒድ 2009 ሐምሌ ወር በቶታል ካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ከደቡብ አፍሪካው ማሜሎዲ ሰንዳውስ ጋር በነበረው የምድብ ጨዋታ ለስድስት ወራት ከሜዳ ያራቀው ጉዳት አጋጥሞታል። ዳግምኛ ለጨዋታ ዝግጁ ሆኖም መጋቢት ላይ በሌላ የቻንፒየንስ ሊግ የምድብ ማጣርያ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከዩጋንዳው ኬሲሲኤ ጋር በአዲስ አበባ ስታድየም ሲገናኝ በመጨረሻ ደቂቃ በአቡበከር ሳኒ ተቀይሮ ቢገባም ብዙም ሳይቆይ የጉልበት ጉዳቱ ዳግም አገርሽቶበት ከሜዳ መውጣቱ ይታወሳል።

ሳላዲን ያለፉትን ስድስት ወራት ከኢትዮጵያ ውጭ በጀርመን ሀገር የተሳካ ህክምና አድርጎ ከተመለሰ ጀምሮ የህክምናው ባለሙያ ባወጣለት የልምምድ ጊዜ መሠረት በጂም እንዲሁም በግሉ የተለያዩ ቀለል ያሉ ልምምዶችን ሲሰራ ከቆየ በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን በሚያደርግበት ቢሸፍቱ በሚገኘው የክቡር ይድነቃቸው ተሰማ እግርኳስ አካዳሚ ሜዳ ከሁሉም የቡድኑ አባላት ጋር ተቀላቅሎ ጠንከር ያለ ልምምድ ማድረግ ጀምሯል። ” አሁን በጣም በጥሩ ሁኔታ ላይ እገኛላው ቀልል ካሉ ልምዶች ወደ ጠንከር ወደአሉ ልምምዶች ተሻግሬአለው። ከፈጣሪ ጋር ህዳር ወር መጀመርያ ላይ ወደ ሜዳ እመለሳለው  ” በማለትም አስተያየቱን ሰጥቷል።