ቫዝ ፒንቶ ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቀጣይ ቆይታቸው ይናገራሉ

የፖርችጋላዊው አሰልጣኝ ቫስ ፒንቶ የፈረሰኞቹ ቤት እጣ ፈንታ በቅርቡ ቁርጡ ይለይለታል።

2010 መስከረም የጣና ሐይቅን ከእንቦጭ አረም ለመታደግ በባህር ዳር ቅዱስ ጊዮርጊስ ከፋሲል ከነማ ባደረጉት የገቢ ማሰባሰቢያ ጨዋታ ነበር ስራቸውን መጀመርያ ያደረጉት። ክለቡ አሰልጣኙን ሲቀጥር በቀጣይ ሊያሳኳቸው ይገባል ብሎ ያስቀመጠላቸው ግቦች ነበሩ። የ2010 ቻንፒዮን መሆን ፣ በካፍ ቶታል ቻምፒየንስ ሊግ ሩብ ፍፃሜ መድረስ፣ ይህ የማይሳካ ከሆነ ደግሞ በካፍ ኮንፌዴሬሽን ካፕ የተሻለ ደረጃ ማድረስ እና ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች ቡድኖችን መከታተል ፣ ድጋፍ ማድረግ እና ለዋናው ቡድን መጋቢ የሆኑ ተጫዋቾችን ማብቃት ዋና ዋና የተቀመጡ ግቦች ነበሩ።

እነዚህን ግቦች እንዲያሳኩ ስምምነት ላይ የደረሱት ቫስ ፒንቶ አንዱንም አለማሳካታቸውን ተከትሎ በደጋፊዎች ዘንድ እምነት አጥተው በተለያዩ መንገዶች ተቃውሞ ሲያስተናግዱ ቀይተዋል። በዚህ ጉዳይ ላይም የክለቡ የቦርድ ሊቀ-መንበር አቶ አብነት ገብረመስቀል ” ሁሉንም ነገር በሚገባ እየመረመርን እየተፈተሸ ነው። ማንም የሚድን ሰው የለም ” ሲሉ መናገራቸው የሚታወስ ነው።

አሰልጣኝ ፒንቶ ስለ ቀጣይ ቆይታቸው ዛሬ የክለቡን ቅድመ ዝግጅት ለመስራት በልምምድ ሜዳ ለተገኘችው ሶከር ኢትዮዽያ በሰጡት አስተያየት ” እኔ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ችግር ነኝ ብዬ ካሰብኩ ቦርዱን ከማነጋገር እና ወደ ሌሎች ሀገሮች ሄጄ ስራዬን ከመቀጠል ወደ ኋላ አልልም። እዚህ ከመምጣቴ በፊት የሰራሁትን አውቃለው ፤ እዚህም የሰራሁትን አውቃለሁ። ስለዚህ የራሴ የወደፊት ዕጣ ፈንታ አያሳስብኝም።” ብለዋል።

ሶከር ኢትዮዽያ ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ምንጮቿ እንዳገኘችው መረጃ ከሆነ አሰልጣኝ ቫዝ ፒንቶ በፈረሰኞቹ ቤት የመቆየታቸው ጉዳይ እያከተመ ሲሆን በቅርቡ በስፖርት ማህበሩ የቦርድ አመራሮች ውሳኔ የሚያገኝ ይሆናል ።