(ይህ ዜና የተላከው ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ህዝብ ግንኙነት ነው)
በ2008 ዓ.ም የውድድር ዘመን በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተካፋይ የሚሆኑት የ14 የእግር ኳስ ክለቦች የእጣ ማውጣት ስነስርዓት መስከረም 21 ቀን 2008 ዓ.ም በተወካዮቻቸው አማካኝነት ይከናወናል፡፡
የእጣ ማውጣት ስነስርዓቱ መስከረም 21/2008 ከጠዋቱ 3፡00 ጀምሮ በካፒታል ሆቴል የሚካሄድ ሲሆን ለውድድር ዘመኑ በተዘጋጀው የውድድር ደንብ ላይ ውይይት በማካሄድ እንደሚያጸድቁት ይጠበቃል፡፡በተጨማሪም በ2007 የውድድር ዘመን አፈጻጻም ላይ ያተኮረ ግምገማ እንደሚካሄድም ለማወቅ ተችሏል፡፡
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እግር ኳስ ክለቦች ከፌዴሬሽኑ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ጋር ነሃሴ 28 ቀን 2007 ዓ.ም በኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል በካሄደት ውይይት የ2008 ዓ.ም ውድድር ከጥቅምት 18/2008 ዓ.ም ጀምሮ እንዲካሄድ መስማማታቸው የሚታወስ ነው፡፡
ፌዴሬሽኑ ውድድሩን በመስከረም ወር መጨረሻ ለማስጀመር ቢያቅድም የየክለቦቹ ተወካዮች የዝግጅት ጊዜ እንደሚያንሳቸው ባቀረቡት ጥያቄና የደረሱበትን የጋራ ስምምነት መሰረት ተከትሎ የእጣ ማውጣት ስነስርአቱን መስከረም 21/2008 ለማካሄድ ለሁሉም የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች በድጋሚ ጥሪ ተላልፎላቸዋል፡፡
ቀደም ሲል የእጣ ማውጣት ስነስርአቱ መስረም 18/2008 እንደሚካሄድ ቢገለጽም የክለቦችን ጥያቄ መሰረት በማድረግና ወቅታዊ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ወደ መስከረም 21/2008 እንዲተላለፍ ተደርጓል፡፡