ቅዱስ ጊዮርጊስ እንግሊዛዊ አሰልጣኝ ቀጠረ

የውድድር ዓመቱን በጥሩ ሁኔታ ያልጀመረው ቅዱስ ጊዮርጊስ ዋና አሰልጣኙ የነበሩት ፖርቱጋላዊው ማኑኤል ቫዝ ፒንቶን ካሰናበተ በኋላ አንድ ጨዋታ በምክትል አሰልጣኙ ዘሪሁን ሸንገታ እየተመራ በባህር ዳር ከተማ መሸነፉ የሚታወስ ሲሆን ከፒንቶ ስንብት ጀምሮ ክለቡን እንደሚረከቡ ሲጠበቁ የቆዩት እንግሊዛዊው ጆን ስቴዋርት ሀልን መቅጠሩን ይፋ አድርጓል።

የ62 ዓመቱ ስቴዋርት በህንዱ ፑኔ ክለብ እና ሴይንት ቪንሰንት እና ግሬናዲንስ ብሔራዊ ቡድን ከሰሩ በኋላ በ2010 ወደ ምስራቅ አፍሪካ በመምጣት የዛንዚባር ብሔራዊ ቡድን፣ የታንዛኒያው አዛም ፣ የኬንያዎቹ ሶፋካፓ እና ሊዮፓርድስ አሰልጥነዋል። ከ2018 ጀምሮ ደግሞ ወደ ባንግላዴሽ አምርተው ሴይፍ ስፖርቲንግ ክለብን ሲያሰለጥኑ ቆይተዋል። አሰልጣኙ በቅዱስ ጊዮርጊስ ስራቸውን በነገው ዕለት እንደሚጀምሩም ተገልጿል።

አሰልጣኝ ስቴዋርት ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከተቀላቀሉ በኋላ ተከታዩን አስተያየት ለክለቡ ይፋዊ የፌስቡክ ገፅ ሰጥተዋል። “በባንግላዴሽ ቆይታዬ ጥሩ ተከፋይ አሰልጣኝ ነበርኩ። በሊጉም ዛሬ እዚህ አስክመጣ ድረስ በ18 ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ሽንፈትን አላስተናገድኩም፡፡ ነገር ግን ለ8 ዓመታት በምስራቅ አፍሪካ በተለያዩ ክለብና ብሔራዊ ቡድኖች ስቆይ ቅዱስ ጊዮርጊስን ማሰልጠን እፈልግ ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ከክለቡ ጥያቄ ሲቀርብልኝ ባሳልፈው የምፀፀትበት ውሳኔ ይሆናል ብዬ የልቀቁን ጥያቄ ለክለቤ አቀረብኩኝ እነርሱም መልቀቅ ባይፈልጉም ጥያቄን ተቀብለውኛል፡፡ ”

ከ1996 ጀምሮ በመደበኛነት የውጪ አሰልጣኞችን እየሾመ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ15 ዓመታት ውሰጥ 11ኛ የውጪ ዜጋ አሰልጣኙን ቀጥሯል።


ተዛማጅ ጽሁፍቅዱስ ጊዮርጊስ ከፖርቱጋላዊ ወደ እንግሊዛዊ ?