የደደቢት ህልውና አስጊ ደረጃ ላይ ደርሷል

ደደቢት እግርኳስ ክለብ በፋይናንስ አቅም ማነስ ምክንያት ህልውናውን የማስቀጠል ፈተና ውስጥ ገብቷል።

በ1989 ተመስርቶ በ2002 ወደ ፕሪምየር ሊግ በማደግ በሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ በመሆን በ2005 የሊጉ ዋንጫ ማንሳት ችሎ የነበረው ደደቢት ያለፉት ሁለት ዓመታት በገንዘብ አቅም መዳከም ምክንያት እየተቸገረ መቆየቱ ይታወሳል። ክረምት ላይ መቀመጫውን ወደ መቐለ በመቀየር የተጫዋቾች ደሞዝ ክፍያን በከፍተኛ መጠን ዝቅ ማድረጉን ያስታወቀውና ውጤታማ የሴት ቡድኑን ያፈረሰው ደደቢት ከለውጦቹ በኋላ የፋይናንስ ችግሩ እንደሚቃለል ቢጠበቅም በአጋር ድርጅቶች እጦት በትልቅ ችግር ውስጥ ይገኛል።

በዚህ ጉዳይ ዙርያ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጠር ያለ ቆይታ ያረጉት የደደቢት ቡድን መሪ አቶ ኤፍሬም አበራ ችግሩን ለመፍታት በሰፊው እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ገልፀው እንደታሰበው ችግሩ የማይፈታ ከሆነ ግን የቡድኑ ህልውና አደጋ ላይ መሆኑን ገልፀዋል። ” ለትግራይ ክልል ም\ርዕሰ መስተዳድር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) ጨምሮ ለሌሎች አጋር ድርጅቶች ደብዳቤ ለመላክ እየተዘጋጀን ነው። ክልሉም ሆነ ድርጅቶች የዚህ ትልቅ ክለብ ህልውናን እንደሚያስቀጥሉ ተስፋ አደርጋለሁ። ችግሩን በዚህ ሁለት ቀን ውስጥ እንፈታዋለን ብለንም ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል።

ደደቢት የዝውውር ፖሊሲውን በመቀየር አዲስ ቡድን ገንብቶ በትግራይ ክልል ዋንጫ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ በማሳየት ሶስተኛ ደረጃ ይዞ ሲያጠናቅቅ በፕሪምየር ሊጉ ሁለቱ የሊጉ መሪዎች መቐለ እና ቡናን ትግራይ ስታድየም ላይ ገጥሞ መሸነፉ ይታወሳል።