የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና የግብፁ ክለብ አል አህሊ ወሳኝ አጥቂ ሳልሃዲን ሰይድ ባጋጠመው ጉዳት ምክኒያት ለ6 ሳምንታት ከሜዳ እንደሚርቅ ክለቡ አስታውቋል። ሳልሃዲን በግብፅ ሱፐር ካፕ ክለቡ ከዛማሌክ ጋር ባደረገው ጨዋታ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሰልፎ በ73ተኛው ደቂቃ በጉዳት ተቀይሮ መውጣቱ ይታወሳል። በዶ/ር ኢሃብ አሊ የሚመራው የአህሊ ህክምና ቡድንም በሳልሃዲን ላይ በርካታ ምርመራዎችን ካደረገ በኋላ ለ6 ሳምንታት ያህል መጫወት እንደማይችል ገልጿል።
ሳልሃዲን ከ3 ሳምንታት በኋላ ከማሊ ጋር የደርሶ መልስ ጨዋታ በሚያደርገው የባሬቶ ስብስብ ውስጥ የተካተተ ሲሆን ለጨዋታው ከጉዳቱ አገግሞ ይደርሳል ተብሎ አይጠበቅም። ሳልሃዲን ከቡድኑ ውጪ የሚሆን ከሆነ በመጨረሻ ሰዓት ከቡድኑ የተቀነሰው ፍፁም ገብረማርያም ሊመለስ ይችላል።