ሪፖርት| የበረከት ይስሀቅ ብቸኛ ግብ ደቡብ ፖሊስን የዓመቱ የመጀመርያ ሶስት ነጥብ አስጨብጧል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 3ኛ ሳምንት ዛሬ አንድ ጨዋታ ሀዋሳ ላይ ተደርጎ ደቡብ ፖሊስ ደደቢትን አስተናግዶ 1-0 በማሸነፍ ከ9 ዓታት በኋላ የመጀመርያ ድሉን አስመዝግቧል። ከሜዳ ውጪ የተቸገረው ደደቢት ደግሞ በሜዳ ላይም ውጤት ለማግኘት ተቸግሯል።

የሁለተኛው ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች በተስተካካይ መርሀ ግብር በመያዙ ደቡብ ፖሊስ ከድሬዳዋ ከተማ በቀሪነት ተይዞለት በአንፃሩ ደደቢት ደግሞ በሜዳው ባደረገው ሁለት ጨወታ በመቐለ እና ኢትዮጵያ ቡና ተረቶ ነበር ሁለቱ ቡድኖች ለዛሬው ጨዋታ የቀረቡት።

ደቡብ ፖሊስ በመጀመሪያው ሳምንት በሜዳው በመከላከያ 2-1 በተረታበት ጨዋታ በነበሩት ዘነበ ከድር፣ ዘላለም ኢሳይያስ እና የተሻ ግዛው ምትክ አበባው ቡጣቆ፣ ሙሉዓለም ረጋሳን እና ኄኖክ አየለን በመጀመርያ አሰላለፍ ውስጥ በማካተት ወደ ሜዳ ሲገባ ከጨዋታው አስቀድሞ በፋይናንስ እጥረት ምክንያት ይህን ጨዋታ እንዲራዘምለት ቢጠይቅም ተቀባይነት ያላገኘው ደደቢት በአንፃሩ በኢትዮጵያ ቡና በተሸነፈበት ጨዋታ ከነበሩ ተጫዋቾች አራቱን ብቻ (ኄኖክ መርሹ፣ ኤፍሬም ጌታቸው፣ አብርሃም ታምራት እና አለምአንተ ካሳን) በመጀመርያ ተሰላፊነት ተጠቅሟል።

በፌዴራል ዳኛ ሐብታሙ መንግስቴ የተመራው የሁለቱ ቡድኖች ጨወታ ሳቢ ያልነበረ ነበር። ባለ ሜዳው ደቡብ ፖሊስ ወደ ቀኝ መስመር ወደ አመዝኖ ለመጫወት ሞክሮ የተሻለ የነበረበት ሲሆን የደደቢት ቅብብሎች በተደጋጋሚ የሚቆራረጡ ነበሩ። የመጀመሪያ የግብ አጋጣሚን ለመመልከት ብዙም ደቂቃ መጠበቅ አላስፈለገም፤ 5ኛው ደቂቃ ላይ የከፍተኛ ሊጉ ኮከብ ተጫዋቾች ብሩክ ኤልያስ በቀኝ በኩል እየገፋ ገብቶ ለኄኖክ አየለ የሰጠውን ኳስ ኄኖክ በሳጥን ውስጥ ጥሩ አቋቋም ላይ ለነበረው አጥቂው በረከት ይስሀቅ አመቻችቶለት በረከት በአዲሱ የደደቢት የውጭ ግብ ጠባቂ ረሺድ ማታውሲ መረብ ላይ አሳርፎ ቢጫ ለባሾቹን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።

ደቡብ ፖሊሶች ከጎሉ መቆጠር በኋላም ተጨማሪ የግብ እድሎችን መፍጠር ቢችሉም በረከት ይስሀቅ እና ኄኖክ አየለ ያገኟቸውን መልካም አጋጣሚዎች በተደጋጋሚ ሲያመክኑ ተስተውሏል። በደደቢት በኩልም በአሌክሳንደር ዐወት እና አብርሀም ታምራት የተሞከሩ ሁለት ሙከራዎች በዚህ አጋማሽ የሚጠቀሱ ናቸው።

በሁለተኛው አጋማሽ ደደቢቶች አጥቂውን አክዌር ቻሞን ቀይረው ካስገቡ በኋላ መጠነኛ መሻሻል በማሳየት ጫና ፈጥረው መጫወት ቢችሉም ጥረታቸው ፍሬ አልባ ሲሆን ተስተውሏል። በዚህም አጋማሽ የተሻሉ የነበሩት ደቡብ ፖሊሶች በበኩላቸው እንደመጀመርያው አጋማሽ ሁሉ በተደጋጋሚ ወደ ደደቢት የግብ ክልል ቢያመሩም ተጨማሪ ጎል ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። 75ኛው ደቂቃ ላይ አበባው ቡጣቆ ለበረከት ይስሀቅ ሰቶት የሳተው እና በ90ኛው ደቂቃ የተሻ ግዛው የግቡ አግዳሚ የመለሰበት አጋጣሚዎችም በጉልህ የሚጠቀሱ ነበሩ። በደደቢት በኩል ደግሞ 60ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ መሐመድ በቀኝ በኩል የሰጠውን ኳስ አክዌር ቢያገኛትም ግብ ጠባቂው ዳዊት አሰፋ ቀድሞ ያስጣለው ኳስ አቻ ሊሆኑ የተቃረቡባት ነበረች።

ጨዋታው በደቡብ ፖሊስ 1-0 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ የሀዋሳው ክለብ የውድድር ዓመቱን የመጀመርያ ድል ሲያስመዘግብ ከሊጉ በወረደበት 2002 የመጨረሻ ሳምንት አዳማ ከተማን ካሸነፈ በኋላ የመጀመርያ ሦስት ነጥቡን አግኝቷል። ደደቢት በአንጻሩ ያደረጋቸውን ሦስት ጨዋታዎች በሙሉ ተሸንፎ አንድም ግብ ሳያስቆጥር በሊጉ ግርጌ ላይ ተቀምጧል።

በጥቂት ተመልካች ታጅቦ የተደረገው ጨዋታ ሁለት የማስጠንቀቂያ ካርዶች በፌዴራል ዳኛ ሐብታሙ መንግስቴ ተመዞበታል።

የጨዋታውን ሙሉ መረጃ ሊንኩን ተጭነው ያገኛሉ፡LINK