የአሰልጣኞች አስተያየት| ደቡብ ፖሊስ 1-0 ደደቢት

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ በተካሄደው ብቸኛ የሦስተኛ ሳምንት ጨዋታ ደቡብ ፖሊስ ደደቢትን 1-0 አሸንፏል። በጨዋታው ዙርያ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች የሰጡትን አስተያየት እነሆ

ዘላለም ሽፈራው – ደቡብ ፖሊስ 

ስለ ጨዋታው

ጨዋታው በእርግጥ ጥሩ ነው፤ ጥሩ የምልበት ምክንያት ሶስት ነጥብ ማግኘት በመቻላችን ነው። ይህ ማለት ግን ሙሉ ነን ማለት አልችልም። በጨዋታው እጅግ በጣም ብዙ የግብ አጋጣሚዎችን ፈጥረናል፤ የመጠቀም አቅማችን ግን ደካማ ነበር። በተለይ ከእረፍት በፊት ፍፁም ያለቀላቸው ኳሶችን አግኝተን አልተጠቀምንም። ከእረፍት በኃላም የማጥቃት አቅማችን ምንም እንኳን እንደመጀመሪያው አጋማሽ ባይሆንም የመጠቀም አቅማችን ያው ደካማ እንደነበር ታይቷል። ይሄ ደግሞ በቁጥር የሚገለፅ ነው። 

ከተቃራኒ ቡድን በኔ በኩል አንድም ሙከራ አልታየኝም። ምናልባት እኛ በምንፈጥራቸው ስህተቶች የሚገኙ የግብ አጋጣሚዎች ለመሄድ ከሚያደርጉት ውጭ ሌላ ነገር አልነበረም። በኛ በኩል በተለይ ከጎል ማስቆጠር ጋር የሚገናኙ ነገሮች ላይ መስራት እንዳለብን ያየንበት የመከላከል አቅማችንም የተደራጀና ጥብቅ እንዳልሆነ የተረዳንበት ነው። ስለዚህ እነዚህ መስተካከል አለባቸው። ምናልባት የተቃራኒ ቡድን አጥቂዎችም ያን ያህል ከባድ አለመሆን ተከላካዮቻችንን ጥሩ አስመስሏቸው ሊሆን ቢችልም መሻሻል ይጠበቅብናል። 

የአጨራረስ ችግር

እንግዲህ ከጨዋታው ተነስተህ ነው ራስህን የምታዘጋጀው። እኛ ባየነው ልክ የአጨራረስ ድክመት እንዳለብን አይተናል። ስለዚህ መስራት ነው፤፤ ከመስራት ጎን ለጎንም አብዛኛውን ስራ የሚወስደው መነጋገሩ ነው። እዛ ቦታ ላይ እንነጋገራለን።


ኤልያስ ኢብራሂም – ደደቢት 

ስለጨዋታው

በጨዋታው የመጀመሪያ አርባ አምስት ደቂቃ ከፀሀዩ ጋር ተደምሮ የሜዳውም ተፅዕኖ ነበረው። ጨዋታው እንደተጀመረ ነው ጎል የተቆጠረብን፤ ወጣቶች ስለሆኑም ትንሽ መደናገሮች ነበሩ። ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታ ለመግባት ሞክረናል። ጥሩ ነው ነው ብዬ የማስበው። ከእረፍት መልስ ወደ አንድ አጨዋወት መምጣት ችለናል። አኩዌር ቻሞ ከጉዳት ነው የተመለሰው፤ ባለፈው በቡና ጨዋታም አልተሰለፈም። ዛሬ ግን ቀይረን አስገብተነው ጥሩ እንቅስቃሴ አድርጓል። በሂደት ደግሞ የተሻለ ነገር እንፈጥራለን። 

ስለ ዛሬው ሽንፈት 

ትኩረት አድርገን እየሰራን ያለነው ወጣቶች ላይ ነው። ከተስፋ ቡድን እና ከወጣት ቡድኖች የመጫወት ዕድል የሌላቸውን ነው ሰብስበን እያጫወትን ያለነው። ወጣቶች ላይ ስትሰራ ብዙ ጊዜ በጊዜ ሂደት ነው ወደ አንድ እንቅስቃሴ የሚገባው። ከዛ አንፃር ሶስት ጨዋታዎችን አድርገን ሶስቱንም ተሸንፈናል። ዋናው ግቡ ያ ሳይሆን ከጨዋታ ጨዋታ ተጫዋቾቹ እንቅስቃሴያቸው ምን ያህል ነው? ቀጣዩስ? የሚለውን ስናየው ከመጀመሪያው የመቐለው ጨዋታ ቀጥሎ ከቡና ከዛም ዛሬ ስናይ የተሻለ ነው። በመሀል የውድድር መቆራረጥ ባይኖር ኖሮ ከቡና ጨዋታ በነበረን መሻሻል ቀጥለን እንሄድ ነበር። ዛሬ ባየነው እንቅስቃሴ የተሻሉ ናቸው፤ በቀጣይም የተሻለ ነገር ሰርተን ወደ አሸናፊነት እንመለሳለን።

የውጤት ቀውስ 

ዛሬ ገና ሶስተኛ ጨዋታችን ነው። እኛ በእቅዳችን መሰረት ከጨዋታ ጨዋታ መሻሻል ነው። ሶስተኛ ሳምንት ላይ ጥሩ ነገር ላይ ነው ያለነው። በቀጣይ ወደ ተሻለ ደረጃ እንደርሳለን፤ መውረድ ግን አይታየኝም። ወጣቶች ስለሆኑ ወደ አንድ ሪትም ሲመጡ የተሻለ ነገር ይኖረናል።