ኢትዮጵያዊያን ዳኞች ለኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ጨዋታ ወደ ዛንዚባር ያመራሉ

የ2018/19 የውድድር ዘመን የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ በይፋ በዚህ ሳምንት ሲጀመር ኢትዮጵያዊያን ዳኞች ወደ ዛንዚባር አምርተው የቅድመ ማጣርያ የመልስ ጨዋታ ይመራሉ። 
የደቡብ አፍሪካው ካይዘር ቺፍስ እና የዛንዚባሩ ዚማሞቶ የሚያደርጉት የመጀመርያ ጨዋታ ሶዌቶ ላይ በዚህ ሳምንት ሲካሄድ የመልሱ ጨዋታ ደግሞ ዛንዚባር ላይ በቀጣይ ሳምንት ይከናወናል። ይህንን የመልስ ጨዋታም አምና ወደ ኢንተርናሽናል ዳኝነት ያደገው ዳዊት አሳምነው በዋና ዳኝነት ሲመራው ክንዴ ሙሴ እና ኃይለራጉኤል ወልዳይ በረዳትነት አብረውት የሚመሩ ይሆናል። በአራተኛ ዳኝነት ደግሞ  አማኑኤል ኃይለሥላሴ አብሮ እንደሚጓዝ ለማወቅ ተችሏል። 

በሌላ ዜና ለሚ ንጉሴ ቻምፒየንስ ሊጉ ቅድመ ማጣርያ ዙር ሁለት ጨዋታዎች ላይ በዋና ዳኝነት እንዲመራ ሲመረጥ ትግል ግዛው፣ ተመስገን ሳሙኤል፣ በላቸው ይታየው፣ በላይ ታደሰ እና በዓምላክ ተሰማ በረዳት እና አራተኛ ዳኝነት መመደባቸው ይታወሳል።