የኢትዮጵያ ሱፐርካፕ ለ3 ተከታታይ የውድድር ዘመናት ከተዘነጋ በኋላ ዛሬ በ10፡00 በፕሪሚየር ሊግ አሸናፊው ቅዱስ ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ዋንጫ አሸናፊው መከላከያ መካከል ይደረጋል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች ከ10 ቀናት በፊት በኢትዮጵያ ዋንጫ ግማሽ ፍፃሜ ተገናኝተው መከላከያ በአዲሱ ተስፋዬ እና በኃይሉ ግርማ ግቦች አሸንፈው ፍፃሜውን መቀላቀላቸው የሚታወስ ነው፡፡ መከላከያ በፍፃሜው ሀዋሳ ከነማን 2-0 አሸንፎ ለዛሬው የሱፐርካፕ ፍልሚያ ደርሷል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ከአስቸጋሪው የ2007 የውድድር ዘመን ጉዞው በኋላ የውድድር ዘመኑን በሊጉ ቻምፒዮንነት ማጠናቀቅ ችሏል፡፡
2007 የፕሪሚየር ሊግ ባለድሉ ቅዱስ ጊዮርጊስ ምክትል አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንጋታ ቡድናቸው ዋንጫውን ለማንሳት እንደተዘጋጀ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡
‹‹ ከባለፈው የመከላከያ ጨዋታ ስህተቶቻችን ብዙ ተምረናል፡፡ ሁልጊዜም በልምምድ ድክመቶቻችንን ለማስተካከል እንጥራለን፡፡ ነገር ግን ባለፈው ስላሸነፉን ብለን የተለየ ዝግጅት አላደረግንም፡፡ ›› ብለዋል፡፡ አሰልጣኙ ጨምረው እንደገለፁት እንደአዲስ ቡድኑን የተቀላቀሉት ተጫዋቾች ለቡድናቸው ተጨማሪ ኃይል እንደሚፈጥርላቸው ተናግረዋል፡፡
‹‹ የሳላዲን ፣ ናትናኤል እና አበባው ቡድናችንን መቀላቀል ተጨማሪ አቅም እንዲኖረን አድርጎልናል፡፡ ይህንን ተጠቅመን የመከላከያውን ጨዋታ በድል ለመወጣ እገባለን፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዋንጫ ፊት ቀርቦ የማይመለስ ክለብ ነው፡፡ ›› ሲሉ ሀሳባቸውን አጠቃለዋል፡፡
ከቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ትላንት የጋብቻ ስነስርአቱን የፈፀመው በኃይሉ አሰፋ ለዛሬው ጨዋታ አይደርስም፡፡ አዲሱ ፈራሚ ራምኬ ሎክ ደግሞ ኢትዮጵያ ከቦትስዋና ባደረገችው ጨዋታ ጉዳት በማስተናገዱ የዛሬው ጨዋታ ያመልጠዋል፡፡ በተቃራኒው አበባው ቡታቆ ከአንድ የውድድር ዘመን በኋላ በቅዱስ ጊዮርጊስ ማልያ ለመታየት ከዘካርያስ ቱጂ ጋር ፉክክር ያደርጋል፡፡
የኢትዮጵያ ዋንጫው ባለድል መከላከያ አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ዋና ግባቸውን ያሳኩት ባለፈው ቅዳሜ በመሆኑ ይህንን ጨዋታ የሚያደርጉት ለክብር ብቻ መሆኑን ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡
‹‹ ዋናው እቅዳችን የነበረው ለአፍሪካ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ማለፍን አሳክተናል፡፡ ይህ ጨዋታ የሚደረገውም ለክብር ብቻ ነው፡፡ ክብራችንን ለማስጠበቅ ወደ ሜዳ እገባለን፡፡ ይበልጥ የተዋሃደ ቡድን ይዘን ለመግባት ጥረት እናደርጋለን›› ብለዋል፡፡ ገ/መድህን በክረምቱ ያስፈረሙት ባዬ ገዛኸኝ እስካሁን ግብ ያለማስቆጠሩን ምክንያትም ተናግረዋል፡፡
‹‹ ባዬ ጥሩ አቅም ያለው ተጫዋች ነው፡፡ ግብ የሚያስቆጥር እና የአካል ብቃቱ የተሟላ ተጫዋች ነው፡፡ ነገር ግን ለቡድናችን የመጀመርያውን ጨዋታ ያደረገው በተቀላቀለ በ10ኛ ቀኑ ነው፡፡ አመዛኙን ጊዜ ያሳለፈው በብሄራዊ ቡድን በመሆኑ ከቡድናችን ጋ እስካሁን የመዋሃጃ ጊዜ አላገኘም ›› ሲሉ ባዬን ተከላክለዋል፡፡
መከላከያ በዛሬው ጨዋታ የተከላካዩ ቴዎድሮስ በቀለን ግልጋሎት በጉዳት ምክንያ አያገኝም፡፡ ቴዎድሮስ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በነበረው ጨዋታ በእጁ ላይ ጉዳት ደርሶበት ተቀይሮ ከሜዳ መውጣቱ ይታወሳል፡፡ ባዬ ገዛኸኝም ከዛሬው ጨዋታ ውጪ ሆኗል፡፡ ባዬ ከብሄራዊ ቡድኑ ጋር በመሆኑ እስካሁን ወደ መከላከያ አለመመለሱን አሰልጣኝ ገብረመድህን ተናግረዋል፡፡ ለረጅም ጊዜ ከሜዳ የራቀው ጀማል ጀማል ጣሰው የዛሬውም ጨዋታ ያመልጠዋል፡፡ በአንጻሩ ያለፉትን ጨዋታዎች በጉዳት ያልተሰለፈው መሃመድ ናስር ከጉዳቱ ሙሉ ለሙሉ አገግሞ ወደ ቋሚ አሰላለፉ ይመለሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የሱፐርካፕ እውነታዎች
-የሊጉ እና የጥሎ ማለፍ አሸናፊ የሚገናኙበት ይህ ውድድር የተጀመረው በ1977 ዓ.ም ነው፡፡ የሊጉ ኮከብ ተጫዋች እና ኮከብ ግብ አግቢ መሸለም የጀመሩትም በዚህ ዘመን ነበር፡፡
-ውድድሩ 24 ጊዜ ሲካሄድ ቅዱስ ጊዮርጊስ በርካታ ዋንጫዎችን በማንሳት ቀዳሚ ነው፡፡ ፈረሰኞቹ ይህንን ዋንጫ ለ13 ጊዜያት ያህል በማንሳት ተወዳዳሪ የላቸውም፡፡ ኢትዮጵያ ቡና 5 ጊዜ በማንሳት ይከተላል፡፡ ኤሌክትሪክ 3 ጊዜ ፣ መከላከያ (ምድር ጦር) 2 ጊዜ ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ (ባንኮች) 1 ጊዜ ዋንጫውን ያነሱ ክለቦች ናቸው፡፡
-1983 ፣ 1984 ፣ 1999 ፣ 2004 ፣ 2005 እና 2006 ውድድሩ ያልተካሄደባቸውና አሸናፊ ያልተመዘገበባቸው ውድድሮች ናቸው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ1991 እና 2001 ፣ ኤሌክትሪክ ደግሞ በ1993 የሊጉ እና የትሎ ማለፉን ዋንጫ በማንሳታቸው ውድድሩ ሳይካሄድ የሱፐርካፕ ዋንጫውን የግላቸው አድርገዋል፡፡
-ሱፐር ካፕ በቀደሙት አመታት የጥሎ ማፉ ወይም የሊጉ ውድድር ከተጠናቀቀ በኋላ በሳምንቱ ይደረግ ነበር፡፡ ከ1990ዎቹ ጀምሮ ደግሞ የሱፐር ካፕ እንደ ውድድር ዘመን መክፈቻ ተቆጥሮ በአዲስ የውድድር ዘን መጀመርያ ላይ መካሄድ ጀምሯል፡፡