‹‹ ቡና የዝውውር ደንቡን ተግባራዊ እያደረገ ያለ ብቸኛ ክለብ ነው›› ገዛኸኝ ወልዴ

ኢትዮጵያ ቡና ዛሬ በብሄራዊ ቴአትር የሬድዮ ፕሮግራሙን አንደኛ አመት በአል ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀው ፕሮግራም ላይ ንግግር ያደረጉት አቶ ገዛኸኝ ወልዴ ስለ አዲሱ የዝውውር ደንብ ንግግር አድርገዋል፡፡

ዘንድሮ ተግባራዊ የተደረገው የዝውውር ደንብን ተግባራዊ ያደረገው ብቸኛ ክለብ ኢትዮጵያ ቡና መሆኑን አቶ ገዣኸኝ በልበ ሙሉነት ተናግረዋል፡፡

‹‹ የዝውውር ደንቡን በትክክል ተግባራዊ እያደረግ ያለው ብቸኛ ክለብ ኢትዮጵያ ቡና ነው ብዬ አፌን ሞልቼ መናገር እችላለሁ፡፡ በፌዴሬሽኑ ህግ ላይ አንድ ተጫዋች እስከ 5 አመት ማስፈረም ይቻላል ቢባልም ክለቦች 2 አመት ብቻ ማስፈረምን እንደ ባህል ወስደውታል፡፡ ከ2 አመት በላይ ቢፈርሙ የሚሞቱ የሚመስላቸው አሉ፡፡ ›› ብለዋል፡፡

አቶ ገዛኸኝ ክለባቸው የሁለት አመት ኮንትራት በማስፈረም ብቻ ቡድኑን በየውድድር ዘመኑ አፍርሶ የመገንባት ሂደት ውስጥ የመግባት ፍላጎት እንደሌላቸውም ተናግረዋል፡፡

‹‹ ቡድናችን በ2 አመት ኮንትራት ምክንያት በየአመቱ እየፈረሰ የሚገነባ ሳይሆን ለሙያቸው ታማኝ የሆኑ ተጫዋቸች ስብስብ እንዲሆኑ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ነው አዳዲስ ተጫዋቾችን የ3 እና 4 አመት ኮንትራት ሰጥተን ያስፈረምናቸው፡፡ ተጫዋቾች ደሞዛቸው የሚከፈላቸው በኮንትራታቸው በተነጋገሩት ብቻ ሳይሆን በየአመቱ በሚያሳዩት አቋም መሻሻል መሰረት ደሞዛቸው ይሻሻላል፡፡ ››

በዛሬው ፕሮግራም የአዲሱ የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ቡና ሙሉ ቡድን ከደጋፊዎቹ ጋር ተዋውቋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *