ሴቶች ፕሪምየር ሊግ| በአንደኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ አርባምንጭ ከተማ አሸንፏል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን የመጀመሪያ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ ዛሬ አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ አርባምንጭ ከተማን ያስተናገደው ቅዱስ ጊዮርጊስ 1ለ0 በሆነ ውጤት ሽንፈትን አስተናግዷል፡፡

እጅግ በጣም ደካማ የሚባል እንቅስቃሴ በታየበት የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ ጨዋታ ለተመልካች አሰልቺ የነበረ እንቅስቃሴ አስመልክቶናል፡፡ በዚሁ አጋማሽ በተለይ በመጨረሻዎቹ 15 ደቂቃዎች እንግዳዎቹ አርባምንጭ ከተማዎች የተሻሉ ነበሩ። በዚህም በ37ኛው ደቂቃ ሰርካለም ባሳ የግብ ማግባት አጋጣሚ ብታገኝም ሳትጠቀምበት ስትቀር በደቂቃዎች ልዩነት በ43ኛው ደቂቃ በተመሳሳይ ያገኘችውን አጋጣሚ ተጠቅማ ክለቧን መሪ ያደረገች ግብ ማስቆጠር ችላለች፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ የህልውናቸው ጉዳይ አደጋ ውስጥ ገብቶ በቅርቡ እልባት ያገኙትና በአዳዲስ ተጫዋቾች ብቅ ያሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከተጋጣሚያቸው በተሻለ ወደ ግብ ለመድረስ ጥረት አድርገዋል፡፡ በተለይም በ63ኛው እና በ65ኛው እንዲሁም በ81ኛው ደቂቃ ላይ ሳራ ዘነበ ከአርባምንጭ ከተማ ግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝታ ያገኘቻቸውን ግልጽ የሆኑ የማግባት አጋጣሚዎችን መጠቀም ሳትችል በመቅረቷ ቡድኗ ከጨዋታው ምንም ነጥብ ሳይዝ ለመውጣት ተገዷል፡፡

የአንደኛ ዲቪዝዮኑ አንደኛ ሳምንት ዛሬ በተካሄደው ጨዋታ ሙሉ ለሙሉ የተጠናቀቀ ሲሆን የሁለተኛው ሳምንት በትላንትናው ዕለት በተካሄደ አንድ ጨዋታ መጀመሩ ይታወሳል። መከላከያ ድሬዳዋ ከተማን ባስተናገደበት ጨዋታም 3-2 ማሸነፍ ችሏል። ለመከላከያ ኤልሳቤጥ ብርሀኑ፣ መዲና ዐወል እና አዲሷ ፈራሚ ሲሳይ ገብረወልድ ሲያስቆጥሩ አዳማን ለቃ በክረምቱ ወደ ድሬዳዋ ያመራችው አይዳ ዑስማን ሁለቱንም የድሬዳዋ ጎሎች አስቆጥራለች።

የደረጃ ሠንጠረዥ፣ ግብ ያስቆጠሩ ተጫዋቾች እና የሁለተኛ ሳምንት ቀጣይ ጨዋታዎች ይህንን ይመስላሉ፡-