ሊዲያ ታፈሰ በ2019 የዓለም ሴቶች ዋንጫ ጨዋታዎች ላይ በዳኝነት እንድትመራ ተመረጠች

በ2019 በፈረንሳይ አስተናጋጅነት የሚደረገው የሴቶች የዓለም ዋንጫ ላይ የሚዳኙ ዳኞች ዝርዝር በዓለም አቀፉ የእግርኳስ አስተዳዳሪ ፊፋ ይፋ ሲደረግ ኢትዮጵያዊቷ አርቢቴር ሊዲያ ታፈሰ ተካታለች።

በተለያዩ ጊዜያት በኢንተርናሽናል መድረክ ላይ እየዳኘች የምትገኘው ሊዲያ ከቀናት በፊት በናይጄሪያ አሸናፊነት በተጠናቀቀው የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ላይ የመክፈቻውን እና ወደ ዓለም ዋንጫ ለማምራት የተደረገ ወሳኝ የግማሽ ፍጻሜን የመራች ሲሆን አሁን ደግሞ የሴቶች እግርኳስ ትልቁ መድረክ የሆነው የዓለም ዋንጫን ለመምራት ከአፍሪካ ከተመረጡ ሦስት የመሐል ዳኞች አንዷ መሆን ችላለች። ሌንግዌ ግላዲስ ከዛምቢያ፤ ሙካንሳንጋ ሳሊማ ከሩዋንዳ ከሊዲያ ጋር የተመረጡ ሌሎች አፍሪካዊያን ዳኞች ሆነዋል።

ሊዲያ በ2015 በካናዳ የዓለም ዋንጫ፣ በ2016 የካሜሩን የአፍሪካ ዋንጫ እና የጆርዳን ከ17 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ፣ በ2018 የፈረንሳይ የዓለም ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ዋንጫ፣ የጋና አፍሪካ ዋንጫ ጨምሮ በርካታ የማጣርያ ውድድሮችን መምራት የቻለች ስኬታማ ዳኛ ናት።

ለስምንተኛ ጊዜ የሚከናወነው የፊፋ የዓለም ሴቶች ዋንጫ ከጁን 7 – ጁላይ 7 በ24 ብሔራዊ ቡድኖች መካከል በዘጠኝ የፈረንሳይ ስታድየሞች ይደረጋሉ። የእጣ ማውጣት ስነ-ስርዓቱም ከአራት ቀናት በኋላ ፓሪስ ላይ እንደሚደረግ ይጠበቃል።