ኮፌድሬሽን ዋንጫ | መከላከያ ለመልሱ ጨዋታ ዛሬ የመጨረሻ ልምምዱን ሰርቷል

በቶታል ካፍ ኮፌድሬሽን 2018/19 ቅድመ ማጣሪያ ጨዋታውን ወደ ናይጄሪያ ተጉዞ በሬንጀርስ ኢተርናሽናል 2 – 0 ሽንፈት የተመለሰው መከላከያ ውጤቱን የመቀልበስ ብርቱ ፈተና ነገ ይጠብቀዋል።
በአራት ዓመት ውስጥ ለሦስተኛ ጊዜ እየተካፈለ የሚገኘው መከላከያ ስፖርት ክለብ የመጀመርያ ጨዋታውን ለማድረግ ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ናይጄሪያ በመጓዝ በሁለተኛው አጋማሽ ጎድዊን አጉዳ ባስቆጠራቸው ሁለት የፍጹም ቅጣት ምት ጎሎች በሬንጀርስ ኢንተርናሽናል 2-0 ተሸንፎ መመለሱ ይታወሳል። ይሄን ውጤት የመቀልበስ ብርቱ ፈተና የሚጠብቀው በአሰልጣኝ ሥዩም ከበደ የሚመራው መከላከያ የመልሱ ጨዋታን ነገ በ10:00 በአዲስ አበባ ስታድየም የሚያደርግ ይሆናል፡፡ ጠንካራ ዝግጅት እያደረገ የቆየው ጦሩ ዛሬ የመጨረሻውን ልምምድ ቀለል ባለ መልኩ ጃንሜዳ በሚገኘው የክለቡ ሜዳ አከናውኗል።

በሬንጀርስ ጨዋታ ላይ በመጀመርያ ተሰላፊነት መጫወት የቻለው አጥቂው ተመስገን ገ/ኪዳን ከናይጄሪያ መልስ በልምምድ ወቅት ባጋጠመው ጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጪ መሆኑ ሲረጋገጥ በእርሱ ምትክ ከአዲስ አበባ ከተማ መከላከያን በዘንድሮ ዓመት የተቀላቀለው አጥቂው ፍቃዱ ዓለሙ ይተካዋል ተብሎ ሲጠበቅ የተቀሩት የቡድኑ ተጫዋቾች በሙሉ በመልካም ጤንነት ላይ ይገኛሉ።

“ጥሩ ዝግጅት አድርገናል ሬንጀርስ ጥሩ ቡድን ነው። ልጆቼ ውጤቱን ቀልብሶ ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ ቁጭት ውስጥ ናቸው። በጥንቃቄ እና በፍጥነት ወደ ጎል በመድረስ ውጤቱን ለመቀልበስ በከፍተኛ ተነሳሽነት ላይ እንገኛል” ሲሉ አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ተናግረዋል።

የናይጄሪያው ሬንጀርስ ከ30 በላይ የልዑካን ቡድን በመያዝ ገና ዛሬ ማምሻውን አዲስአበባ የሚገባ መሆኑ አስገራሚ ሲሆን ይህም የመሆኑ ምክንያት አየሩ እንዳይከብዳቸው በቀጥታ ወደ ጨዋታ ለመግባት አስበው እንደሆነ መገመት ይቻላል። ነገ 10:00 በአዲስ አበባ ስቴዲየም የሚካሄደውን የመልስ ጨዋታ ሩዋንዳውያን ዳኞች ሲዳኙት የጨዋታው ኮሚሽነር ከኬንያ ናቸው።

መከላከያ ውጤቱን በመቀልበስ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ የሚችል ከሆነ የአልጄርያው ቤል አቤስ እና የላይቤርያው ኤልአሲአር አሸናፊን የሚገጥም ይሆናል፡፡

-ፎቶዎቹ ትላንት በአዲስ አበባ ስታዲየም ከተደረገ የልምምድ መርሐ ግብር ላይ የተወሰደ ነው።