የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ2018ቱ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የሳኦቶሜ አቻውን ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም 3-0 በማሸነፍ 3-1 በሆነ ድምር ውጤት ቀጣዩን ዙር መቀላቀል ችሏል። በጨዋታው ሙሉ የበላይነት ለነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዳዊት ፍቃዱ፣ ጋቶች ፓኖም እና ራምኬል ሎክ የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል።
ከጨዋታው በኋላ በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ አሠልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው በርካታ ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል።
“በጨዋታው እንደተመለከታችሁት አሳማኝ በሆነ ጨዋታ ብሔራዊ ቡድኑ አሸንፏል። ተጋጣሚያችን በመጀመሪያው ጨዋታ አስቸግረውን ነበር፤ ሜዳው በጣም ጠባብ ስለነበረ (100 በ50 ነበር)፣ አርቴፊሺያል ሜዳ ስለነበረ አስቸግረውን ነበር፤ በእውነት 3ትም 4ትም ማግባት ይችሉ ነበር፤ በግል ችሎታም፣ በጉልበትም፣ በፍጥነትም 100 በ 100 ተበልጠን ነበር። በዚህ ጨዋታ ግን ብዙም የሞከሩብንም ነገር የለም። በመጀመሪያ ጨዋታ ላይ ስላየናቸው ምን ማድረግ እንደሚገባን በደንብ ተነጋግረናል። ልጆቹ ጋር አንድ ነገር ሰርተን ማሳየት አለብን የሚል እልህ ስለነበረ በፍላጎት ተጫውተው አሸንፈዋል። በኔ ግምት ተጨማሪም ጎል ማግባት እንችል ነበር። እንደነ ራምኬል እና አስቻለው ያሉት ተጫዋቾቻችን ገና ልምድ እያገኙ ያሉ ስለሆኑ ዕድሎቹን መጠቀም አልቻሉም።”
አሠልጣኝ ዮሐንስ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በጨዋታው ያገኘውን በርካታ የግብ አጋጣሚዎች መጠቀም ባለመቻሉ ዙሪያ ተጠይቀው ሲመልሱ
“ቡድኑ ዘጠና በመቶ አዲስ ነው። ከሰውነት ቢሻው ቡድን ሁለት ተጫዋቾች ብቻ ናቸው የቀሩት (ሽመልስ እና ስዩም)። እንደ ቢንያም በላይ ያለ አንድም ጊዜ በፕሪምየር ሊጉ ተጫውቶ የማያውቅ ተጫዋችም በዚህ ወሳኝ ጨዋታ ላይ ተጠቅመናል። እነ ሳልሃዲን እና ጌታነህም መጀመሪያ ለብሔራዊ ቡድኑ ሲጫወቱ በርካታ ዕድሎችን ያባክኑ ነበር፤ በኋላ ልምድ እያገኙ ሲመጡ ነው ግብ ማስቆጠር የጀመሩት። ስለዚህ ያን ሁሉ ጫና ተቆጣጥረው እንደዚህ አይነት ጨዋታ በመጫዎታቸው ልጆቹ ከመወቀስ ይልቅ መመስገን ይገባቸዋል፤” ብለዋል።
ጨዋታውን ለመከታተል በአዲስ አበባ ስታዲየም የተገኘው ተመልካች በቡድኑ ሳይካተቱ የቀሩትን የሳልሃዲን ሰይድ እና ጌታነህ ከበደን ስም እያነሳ ተቃውሞውን ሲያሰማ ታይቷል። የሁለቱ አጥቂዎች ከቡድኑ መቀነስ ከወቅታዊ አቋማቸው ጋር የተያያዘ እንደሆነ አሠልጣኙ አስረድተዋል።
“ብሔራዊ ቡድን የማንም ርስት አይደለም። እነ ሳልሃዲን እና ጌታነህ ቡድኑ ውስጥ እንዳይካተቱ ያደረጋቸው አቅማቸው ነው። በፊት ሃገራችን ውስጥ አጥቂ ስለሌለ የነሱን ልምድ መጠቀም አለብን ብዬ እንደተናገርኩኝ አስታውሳለሁ። ምንም አይነት የፊፋ ካሌንደር የሚከተል የወዳጅነት ጨዋታ ማድረግ ባለመቻላችን ከሃገር ውጪ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ያሉበትን ደረጃ ማወቅ አልቻልንም። በሲሼልስ ጨዋታ ሜዳ ውስጥ ስናያቸው ጎል ከመሳት በተጨማሪ ሌሎች እንቅስቃሴዎቻቸው አጥጋቢ ሆኖ አላገኘሁትም። በየክለቦቻቸውም በተቀያሪ ወንበር ላይ ነበር ጨዋታዎችን ሲያሳልፉ የነበሩት፤ በዚህ ምክኒያት ተጫዋቾቹን ቡድኑ ውስጥ አላካተትኳቸውም። ካሉት ልጆች ጋራ ተወዳድረው ተሸለው ከተገኙ ግን ይሄ ብሔራዊ ቡድን ለማንም ክፍት ነው።”
“ህዝቡ ባሰማው ተቃውሞ ዙሪያ ኢትዮጵያ ዮሐንስ ሳህሌ አይደለችም፤ የሁላችንም ነች። እነዚህ ልጆች የኢትዮጵያን ባንዲራ ለብሰው ሜዳ ውስጥ ገብተው 3-0 እያሸነፉ የሚጮህ ከሆነ፣ የግለሰብ ስም የሚጠራ ከሆነ ይህ ኢትዮጵያዊነት አይደለም። ቡድኑ 3-0 እየመራ እንደዚህ አይነት ነገር ከተፈጠረ እግርኳሳዊ ያልሆነ ድብቅ ዓላማ ያለው ነገር ነው።”
ብሔራዊ ቡድኑ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያው ሁለተኛ ዙር ከኮንጎ ብሔራዊ ቡድን ጋር የሚጫወት ሲሆን የደርሶ መልስ ጨዋታውን የሚያሸንፍ ከሆነም 20 ቡድኖች የሚሳተፉበትን የመጨረሻ የምድብ ማጣሪያ ይቀላቀላል።