ተካልኝ ለቡሩንዲው ጨዋታ አይደርስም ፣ የስዩም እና ዘካርያስም አጠራጣሪ ሆኗል

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በቻን ማጣርያ ከቡሩንዲ ጋር ለሚያደርገው ጨዋታ 25 የልኡካን ቡድ ይዞ ነገ ወደ ቡጁምቡራ ያቀናል፡፡ ቅዳሜ ጨዋታውን ያደርጋል ተብሎም ይጠበቃል፡፡

አሰልጣን ዮሃንስ ሳህሌ ባለፈው እሁድ ሳኦቶሜን ካሸነፈው ቡድናቸው ሽመልስ በቀለን ቀንሰው (በዚህ ውድድር ላይ መጫወት ስለማይችል) የቅዱስ ጊዮርጊሶቹን ሳላዲን በርጊቾ እና ዘካርያስ ቱጂ እንዲሁም የመከላከያውን ምንይሉ ወንድሙን አካተው እየተዘጋጁ ነው፡፡

ሳላዲን በርጊቾ በዲሲፕሊን ቅጣት ያለፉትን 5 የብሄራዊ ጨዋታዎች (የወዳጅነት ጨምሮ) ሳይመረጥ የተዘለለ ሲሆን ዘካርያስ ቱጂ ደግሞ ወደ ሳኦቶሜ ካቀናው ቡድን የተቀነሰ ተጫዋች ነው፡፡

ቡድኑ ዛሬ ረፋድ ልምምዱን ያደረገ ሲሆን ተከላካዮቹ ስዩም ተስፋዬ ፣ ተካልኝ ደጀኔ እና ዘካርያስ ቱጂ ግን ከቡድኑ ጋር ልምምድ አልሰሩም፡፡ የቡድኑ ወጌሻ አቶ በኃይሉ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁት ሶስቱ ተጫዋቾች መጠነኛ ጉዳት የደረሰባቸው በመሆኑ እረፍት ያስፈልጋቸዋል፡፡ በቡሩንዲ ለሚደረገው ጨዋታም አይደርሱም ብለዋል፡፡

የህዝብ ግንኙነቱ አቶ ወንድምኩን አላዩ በበኩላቸው እስካሁን ወደ ቡሩንዲ እንደማይሄድ የተረጋገጠው ተካልኝ ደጀኔ ብቻ ሲሆን ስዩም እና ዘካርያስ ግን አብረው ይጓዛሉ ብለዋል፡፡

ተካልኝ ከሳኦቶሜ ጋር በነበረው ጨዋታ ጉዳት ደርሶበት ተቀይሮ መውጣቱ የሚታወስ ሲሆን በዛሬው ልምምድ ላይ ሙጂብ ቃሲም በቀኝ መስመር ተከላካይ ላይ ሲለማመድ በመስተዋሉ የስዩምን ቦታ ሸፍኖ ሊጫወት ይችላል፡፡

ዘካርያስ እና እና አምበሉ ስዩም በጉዳት የማይጫወቱ ከሆነ ብሄራዊ ቡድናችን በስብስብ ውስጥ በቀኝ እና በግራ መስመር ተከላካይ ስፍራ የሚጫወት ተፈጥሯዊ የቦታው ተጫዋች ሳይዝ ወደ ስፍራው ለማምራት ይገደዳል፡፡ የስዩምን አምበልነት ተረክቦ ቡድኑን የሚመራ አዲስ አምበልም ቅዳሜ እንመለከታለን፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *