አንዳንድ ነጥቦች በቡሩንዲ ብሄራዊ ቡድን ዙሪያ

ዛሬ ከሰዓት ቡጁምቡራ ላይ የቡሩንዲ ብሄራዊ ብድን ከኢትዮጵያ ጋር ሩዋንዳ ለምታዘጋጀው የቻን 2016 ለማለፍ የመጨረሻ ማጣሪያ ግጥሚያውን ያደርጋል፡፡ ብሩንዲ ባሳለፍነው ሳምንት በአለም ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ ሲሸልስን 3-0 በሆነ አጠቃላይ ውጤት አሸንፏል፡፡ በጨዋታው ላይ የነበሩ አብዛኞቹ ተሰላፊዎች ዛሬ ኢትዮጵያን ይገጥማሉ፡፡ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በሴኔጋል 3-1 የተሸነፈው ብሄራዊ ቡድኑ፤ በዛ ጨዋታ ላይ አንድ በውጪ የሚጫወት ተጫዋች ብቻ ይዞ ነበር፡፡ ይህም የሚያሳየው ብድኑ ከሞላ ጎደል በሃገር ውስጥ ተጫዋቾች የተዋቀረ መሆኑን ነው፡፡
ቡሩንዲ በመጀመሪያው ማጣሪያ ጎረቤት ጂቡቲን 4-1 አሸንፋለች፡፡ ቡድኑ ለረጅም ግዜ አንድ ላይ ስለነበረ የቅንጅት ችግር እንደሌለበት አስተያየቱን ለሶከር ኢትዮጵያ የሰጠው የakeza.net ቡሩንዲያዊው የስፓርት ዘጋቢ አርማንድ ንሳቡዌ ይናገራል፡፡
“የቡሩንዲ ብሄራዊ ብድን ኢትዮጵያ የማሸነፍ አቅም አለው፡፡ በርግጥ አሁን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ብድን ያለበት አቋም አላውቅም ነገር ግን ቡሩንዲ ጨዋታውን ለማሸነፍ በሚገባ ተዘጋጅታለች፡፡ በሳለፍነው ጥቂት ሳምንታት ጨዋታዎች ስለነበሩ ብድኑ በጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ለረጅም ግዜ አንድ ላይ የተጫወቱ ተጫዋቾች ስላሉን የቅንጅት ችግር አያሰጋንም፡፡”
ብሩንዲ በብሄራዊ ብድኗ ላይ ወሳኝ ሚና የሚጫወቱት ተጫዋቾቿ ከሊጉ የወቅቱ ሻምፒዮን ቪታሎ ክለብ የተመረጡ ናቸው፡፡ ቪታሎ በቅርቡ የተጀመረው ሊግንም በመምራት ላይ ይገኛል፡፡ ግብ ጠባቂው አርካዛ ማርአርተር፣ ተከላካዮቹ ኢሳ ሃኪዚማና፣ ኪዛ ፋታኪ እና ዴቪድ ኒሺሚሪማና፣ አማካዮቹ ሻሺር ናሂማና እና ባሬንጋ ፒቲስ የቡሩንዲ ወሳኝ ተጫዋቾች ናቸው፡፡ ተጫዋቾቹ የቪታሎ ክለብም ተጫዋቾች ናቸው፡፡ የዋናው ብሄራዊ ብድን ቋሚ ተሰላፊዎች ናቸው፡፡
አርማንድ ንሳቡዌ እንደሚናገረው ከሆነ ብሩንዲ ከሁለት ዓመት በፊት ያሳካችው የቻን ውድድር ላይ መሳተፍ ትችላለች፡፡ በ2014 በደቡብ አፍሪካ በተዘጋጀው ቻን ውድድር ላይ ቡድኑ ተሳተፊ ነበር፡፡
“ሁሉም ነገር ይቻላል፡፡ ተጫዋቾቹ በጥሩ መነሳሳት ላይ ይገኛሉ፡፡ እናውቃለን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ብድን ጠንካራ ተጋጣሚ ሊሆን እንደሚችል፡፡ ተጫዋቾቻን በአፍሪካ ደረጃ ለመታየት ይህን የቻን ውድድር በጣም ይፈልጉታል፡፡ ይህንንም ለማሳካት ኢትዮጵያን ማሸነፍ ግድ ይላል፡፡”

ABDELMALEK
የቡሩንዲ ብሄራዊ ብድን በአልጀሪያዊው አቼን አይት አብደልማሊክ ይሰለጥናል፡፡ አብደልማሊክ ጀርመን የተወለዱ ሲሆን በዜግነት አልጄሪያዊ ናቸው፡፡ አብደልማሊክ ብሩንዲን ለሁለት ዓመት ለማሰልጠን በመጋቢት 2015 ነበር ከስምምነት የደረሱት፡፡ ከሳቸው በፊት አልጄሪያዊው አድል አርሙቺ ከ2008-15 የብሄራዊ ብድኑ አሰልጣኝ ነበሩ (አርሙቺ ኬንያንም አሰልጥነዋል)፡፡ በ44 ዓመቱ አሰልጣኝ ስር ቡሩንዲ 9 ጨዋታዎች ተጫውታለች፡፡ በአምስቱ ድል ሲቀናቸው፤ በሶስቱ ተሸንፈዋል፡፡ አንድ ጨዋታ አቻ ወጥተዋል፡፡ አሰልጣኙ የማሊውን ታላቅ ክለብ ጆሊባ አትሌቲክ ክለብን ለሁለት ዓመት አሰልጥነዋል፡፡ አብዛኛውን ግዜ 4-1-4-1 አሰላለፍ እንደሚመርጡ ይነገራል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *