ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ደቡብ ፖሊስ ከ ባህር ዳር ከተማ

ሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ ላይ የሚደረገው የደቡብ ፖሊስ እና ባህር ዳር ከተማ ጨዋታን የተመለከትንበት ቅድመ ዳሰሳችንን እነሆ።

ከሶዶ በሽንፈት የተመለሰው ደቡብ ፖሊስ ኢትዮጵያ ቡናን የረታው ባህር ዳር ከተማን የሚያስተናግድበት ጨዋታ 08፡00 ላይ በሀዋሳው ሰውሰራሽ ሜዳ ላይ ይከናወናል። ከፍተኛ ሊጉን በቻምፒዮንነት ጨርሰው ቢመጡም ከበርካታ ለውጦች በኋላ የጀመሩት ፕሪምየር ሊጉ ያልቀለላቸው ደቡብ ፖሊሶች አሁንም ከደደቢት በላይ ቢቀመጡም ደረጃቸውን ከዛ በላይ ማሻሻል አልቻሉም። ሳምንት በወላይታ ድቻ የተሸነፉበት ጨዋታም አራተኛ ሽንፈታቸው ሆኗል። ከዚህ በተለየ ሁኔታ አንዴም ሽንፈት ካልገጠማቸው ሦስት ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ባህር ዳር ከተማ ደግሞ ሁለቱን የአዲስ አበባ ክለቦች በመርታት የመጀመሪያ የፕሪምየር ሊግ አጀማመሩን ከፋሲል ከነማ ጋር አመሳስሏል። አምስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት የጣና ሞገዶች አራት ነጥብ ይዘው ከተመለሱባቸው ሁለት የሜዳ ጨዋታዎች በኋላ ነው ደቡብ ፖሊስን የሚገጥሙት። ጨዋታው ከሲዳማ ነጥብ ከተጋሩ በኋላ ሀዋሳ ላይ የሚያደርጉት ሁለተኛ ጨዋታቸውም ጭምር ነው።

በጨዋታው ደቡብ ፖሊስ ከጉዳት የተመለሱ ተከላካዮቹ ጋናዊው አዳሙ መሀመድ እና ደስታ ጌቻሞን አገልግሎት ሲያገኝ የቀኝ ተከላካዩን ብርሀኑ በቀለን ግን በጉዳት ሳቢያ ያጣል። ከዚህ በተጨማሪ በክለቡ ቅጣት ተላልፎበት የነበረው በረከት ይስሀቅም ወደ ሜዳ እንደሚመለስ ይጠበቃል። በባህር ዳር በኩል በልምምድ ወቅት በተከሰተ መጠነኛ ጉዳት እስካሁን ምንም የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ያላከናወነው ሃሪሰን ሄሱ ከጉዳቱ በሚፈለገው ደረጃ ያላገገመ ከመሆኑ በቀር ተጨማሪ የጉዳትም ሆነ የቅጣት ዜና የለም። በሌላ በኩል ክለቡ በከፍተኛ ሊግ ሳለ ቅጣት ተላልፎበት የነበረው ዳግማዊ ሙሉጌታ ቅጣቱን በመጨረሱ ለጨዋታው ብቁ መሆኑ ተነግሯል።

ተለዋዋጭ የተጫዋቾች ምርጫን እየተጠቀመ ያለው ደቡብ ፖሊስ የመጀመሪያ ተሰላፊዎቹን ለመለየት የተቸገር ይመስላል። የቡድኑ ከውጤት መራቅም ለዚህ ዋነኛው ምክንያት ተደርጎ ይወሰዳል። ግብ ከማስቆጠር ባለፈ በርካታ የመጨረሻ ዕድሎችን ለመፍጠር የሚቸገረው ደቡብ ፖሊስ በነገውም ጨዋታ ይህን ኃላፊነት በዋነኝነት ለመስመር አጥቂዎቹ የሚሰጥበት ዕድል የሰፋ ነው። በመሆኑም በነገው ጨዋታ መስፍን እና ብሩክ ከባህርዳር የመስመር ተከላካዮች ጋር የሚኖረውን ፍልሚያ በማሸነፍ ከአማካይ ክፍላቸው ከሚደርሳቸው ኳሶች የግብ ዕድሎችን የመፍጠር ኃላፊነት ይኖርባቸዋል። በዚሁ ቦታ ላይ ከወሰኑ ዓሊ ጥሩ ግልጋሎት እያገኙ የሚገኙት ባህር ዳሮችም በመስመር በኩል ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ለመግባትን ምርጫቸው የሚያደርጉ ይመስላል። ከደቡብ ፖሊስ በተለየ የግብ ዕድሎችን እየፈጠረ ወደ ግብ ምለወጥ ላይ ተዳክሞ የሚታየው ባህር ዳር ነገ ከፊት አጥቂው ጃኮ አታፋት እና ከመስመር አጥቂዎቹ በተጨማሪ የማጥቃት ባህሪ ካላቸው አማካዮቹም ጎሎችን ይጠብቃል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ጨዋታው ለሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያው የፕሪምየር ሊግ ግንኙነታቸው ይሆናል።

– አምና የከፍተኛ ሊጉ ተወዳዳሪዎች የነበሩት ሁለቱ ክለቦች የየምድባቸው አሸናፊ ሆነው የተገናኙበትን የፍፃሜ ጨዋታ ነሐሴ 30 ተከናውኖ ደቡብ ፖሊስ 1-0 ማሸነፍ ችሏል።

– ደቡብ ፖሊስ ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ግብ ያልቀናው ሲሆን በጫወታ አንድ አንድ ግቦችን አስተናግዶም ለሽንፈት ተዳርጓል።

– ባህር ዳር ከተማ እስካሁን ካደረጋቸው አራት ጨዋታዎች ውስጥ ግብ የተቆጠረበት በአንዱ ላይ ብቻ ሲሆን ኳስ እና መረብን ያላገነኛውም በተመሳሳይ በአንድ አጋጣሚ ብቻ ነው።

ዳኛ

– በመጀመሪያው ሳምንት ስሑል ሽረ እና ወላይታ ድቻ የተገናኙበት ጨዋታ ላይ አራት የማስጠንቀቂያ ካርዶችን በመምዘዝ የዘንድሮው የዳኝነት ጉዞውን የጀመረው ወልዴ ንዳው ይህን ጨዋታ ይመራዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ደቡብ ፖሊስ (4-3-3)

ዳዊት አሰፋ

ዘነበ ከድር  – ዘሪሁን አንሸቦ – አዳሙ መሀመድ – አበባው ቡታቆ

ኄኖክ አየለ – ኤርሚያስ በላይ – ሙሉዓለም ረጋሳ

መስፍን ኪዳኔ  – በኃይሉ ወገኔ – ብሩክ ኤልያስ

ባህርዳር ከተማ (4-3-3)

ምንተስኖት አሎ

ሣለአምላክ ተገኝ – ወንድሜነህ ደረጄ  – አቤል ውዱ – አስናቀ ሞገስ

ዳንኤል ኃይሉ  –  ፍቅረሚካኤል ዓለሙ – ኤልያስ አህመድ

ወሰኑ ዓሊ – ጃኮ አራፋት –ግርማ ዲሳሳ