የአሰልጣኞች አስተያየት | ” የድሉ መታሰብያነት ለመላው ደጋፊዎቻችን ይሁን። ” ፀጋዬ ኪዳነማርያም

ወልዋሎ ዓ/ዩ ደደቢትን 1-0 ከረታበት የስድስተኛ ሳምንት የሊጉ የዛሬ ጨዋታ በኋላ በሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ተከታዮቹ አስተያየቶች ተሰጥተዋል።

” በውጤቱ በጣም ደስ ብሎኛል። ደጋፊዎቻችን ዘጠና ደቂቃ ሙሉ ላደረጉልን ድጋፍ እናመሰግናለን። ” ፀጋዬ ኪዳነ ማርያም – ወልዋሎ ዓ/ዩ

ስለጨዋታው…

” ጨዋታው ጥሩ ነበር ፤ በሁለቱም አጋማሾች ተጭነን ለመጫወት ሞክረናል። ተጋጣሚያችን ደደቢትም ኳስን ተቆጣጥረው ለመጫወት ጥረት እያደረጉ ነበር። የያዙት ደረጃ እና ሜዳ ላይ ያሳዩት ብቃት ብዙ ልዩነት ነበረው።

እኛን ባለፉት አራት ጨዋታዎች ማሳካት ካለብን አስራ ሁለት ነጥብ አስሩን አሳክተናል። ይህ ቡድናችን ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሉን ነው የሚያሳየው። ሆኖም አልፎ አልፎ አጨራረስ ላይ ችግር አለብን እሱ በጊዜ ሂደት የሚስተካከል ነው።”

ስለቡድኑ ሁኔታ…

” አሁን ሰባተኛ ሳምንት ላይ ነው ያለነው ፤ ቡድናችን በጥሩ ሁኔታ ላይ ነው ያለው። ይህ ማለት ግን ሙሉ በሙሉ ተሰርቷል ማለት አደለም። ያለብንን ክፍተት ማሰተካከል ይጠበቅብናል። በውጤቱ በጣም ደስ ብሎኛል ደጋፊዎቻችን ዘጠና ደቂቃ ሙሉ ላደረጉልን  ድጋፍ እናመሰግናለን። የድሉ መታሰብያነት ለመላው ደጋፊዎቻችን ይሁን።”

” ለዚህ ጨዋታ በአጠቃላይም ለውድድሩ ትኩረት ሰጥተን ነበር የተዘጋጀነው። ” ኤልያስ ኢብራሂም – ደደቢት

ስለጨዋታው…

” በተከታታይ ጨዋታዎች ተሸንፈን ነው የመጣነው ፤ ለዚህ ጨዋታ በአጠቃላይም ለውድድሩ ትኩረት ሰጥተን ነበር የተዘጋጀነው። በተለይም በዚህ ጨዋታ ሦስት ነጥብ ለመውሰድ ነበር የገባነው ፤ ነገር ግን እንዳያችሁት በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ተጋጣሚያችን እኛ ላይ ጫና ፈጥሮ ነበር። ሆኖም ጫናውን ተቋቁመን ወደ ራሳችን የጨዋታ ቅኝት በመግባት በመጀመርያው አጋማሽ ጥሩ ተንቀሳቅናል። በሁለተኛው አጋማሽም ተጫዋቾች በመቀየር የተሻለ ተንቀሳቅሰናል። ተጋጣሚያችን በአንፃሩ በረጃጅም ኳስ እና በአጋጣሚ በሚገኙ ኳሶች ነበር ሲጥር የነበረው። በዛ መሀል ባለቀ ሰዓት ጎል ተቆጥሮብናል ፤ ያህም ያጋጥማል። ኳስ በነዚህ ሂደቶች ነው የሚያልፈው። “