ሪፖርት | ሀዋሳ ከተማ ግማሽ ደርዘን ግብ አስቆጥሮ ሽረን በመርታት መሪነቱን አጠናክሯል

ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 7ኛ ሳምንት ጨዋታዎች መካከል ሀዋሳ ላይ ሀዋሳ ከተማ ስሑል ሽረን 6-1 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፏል።

የሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ ዛሬ በሁለተኝነት ባስተናገደው በዚህ ጨዋታ ሀዋሳ ወደ አዲስ አበባ አቅንቶ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያለግብ ባጠናቀቀው ጨዋታ ላይ ከተጠቀመባቸው ተጫዋቾች ውስጥ ግብ ጠባቂው ሶሆሆ ሜንሳህን በተክለማርያም ሻንቆ እንዲሁም ያለፉትን አራት ጨዋታዎች ቅጣት ላይ የነበረው አዳነ ግርማን በደስታ ዮሃንስ በመቀየር ወደ ሜዳ አስገብቷል። በስሑል ሽረዎች በኩል ደግሞ ከሲዳማ ቡና ጋር አንድ አቻ ከተለያየው ስብስብ ውስጥ አብዱሰላም አማንን በጅላሎ ሻፊ በመቀየር ብቻ ነበር ጨዋታውን የጀመሩት።

የመጀመሪያው ጨዋታ በጊዜ ባለመጠናቀቁ ምክንያት ይህ ጨዋታ ከተያዘለት ጊዜ 20 ደቂቃዎችን ዘግይቶ ነበር የጀመረው። ጨዋታው ከግቦቹ መብዛት በዘለለ በርካታ አወዛጋቢ የሆኑ የዳኝነት ውሳኔዎችን የተመለከትንበት ነበር። የመጀመሪያው አጋማሽ በተለይ ለ25 ደቂቃዎች ያህል እጅግ አሰልቺ ሊባል የሚችል ጨዋታ የታየበት ሲሆን የሚቆራረጡ ቅብብሎችም የበዙበት ነበር። ይሁንና ገና በጊዜ እንግዳው ቡድን ሽረ ግብ በማስቆጠሩ ቀዳሚ ሆኗል። 5ኛው ደቂቃ ላይ ኪዳኔ አሰፋ በቀኝ በኩል ያሻገራትን ኳስ በሚገባ የተቆጣጠረው አጥቂው ሚድ ፎፋና ነበር ኳስ እና መረብን ማገናኘት የቻለው። በዚህች ግብ የተነቃቁ የመሰሉት ሽረዎች ለትንሽ ደቂቃም ቢሆን ብልጫን የወሰዱበትን እንቅስቃሴ ማድረግ ችለዋል። ሀዋሳ ከተማዎች ግብ እስከሚያስቆጥሩበት ደቂቃ ድረስም ከመሀል ሜዳ ተሻጋሪ ኳሶችን ለመጠቀም ቢሞክሩም ግብ ጠባቂው ሰንደይ ሮቲና በቀላሉ ሲያድንባቸው ቆይቷል።  

39ኛው ደቂቃ ላይ የጨዋታውን አካሄድ የቀየረ ክስተት ተፈጥሯል። ስሑል ሽረዎች በግብ ክልላቸው የቅጣት ምት ሲያገኙ አምበሉ ዲሜጥሮስ ወልደስላሴ ለመምታት በመዘግየቱ የዕለቱ ዳኛ ኢሳያስ ታደሰ ቢጫ ካርድ ካሳዩት በኋላ ያልተገባ ነገር ተናግሮኛል በሚል በሁለተኛ ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ አስወጥተውታል። የስሑል ሽረ አሰልጣኞች እና ተጫዋቾች ዳኛውን በመክበብ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡ ከቀይ ካርዱ በኋላ ሽረዎች አፈግፍገው በአምስት ተከላካዮች የተጫወቱ ቢሆንም  ሀዋሳዎች ዕእረፍት መውጫ ሰአታት ላይ በተጫዋች ቅያሪያቸው ታግዘው አከታትለው ሁለት ግቦችን አስቆጥረዋል። 

ሀዋሳዎች በቀኝ መስመር ላይ ለግቡ መቆጠር ምክንያት የነበረው እና በእንቅስቃሴ ደካማ የነበረውን አክሊሉ ተፈራን በጉዳት ተጠባባቂ በነበረው ደስታ ዮሀንስ ከቀየሩ በኃላ ፍፁም ብልጫን አሳይተዋል። በዚህም ሂደት ውስጥ 44ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ደስታ በግራ በኩል የሰንደይን መዘናጋት ተመልክቶ ግብ አስቆጥሮ ሀዋሳን አቻ ማድረግ ችሏል። ከአንድ ደቂቃ በኃላ ደግሞ በቀኝ በኩል ዳንኤል ደርቤ ወደ ሳጥን ገብቶ አስደናቂ ግብ አስቆጥሮ ባለሜዳዎቹ ከመመራት ተነስተው መሪ ያደረጋቸውን አጋጣሚም ፈጥሮላቸዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ከግቦች ባሻገር የሀይቆቹን የበላይነት እና የስሑል ሽረዎች ደካማ የአጨዋወት መንገድ ከመጀመሪያው አጋማሽ በወረደ መልኩ ሆኖ የተመለከትንበት ነበር። ሀዋሳዎች ገና በጊዜ ነበር ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር የቻሉት። ተቀይሮ በመግባት ልዩነት ሲፈጥር የነበረው ደስታ ዮሀንስ በግራ በኩል ያሻገረውን ኳስ እስራኤል እሸቱ አግኝቷት ነፃ አቋቋም ላይ ለነበረው ታፈሰ ሰለሞን ሰጥቶት ታፈሰ ወደግብነት ቀይሯት የሀዋሳን የግብ መጠን ወደ ሶስት ከፍ ማድረግ ችሏል። 59ኛው ደቂቃ ላይም በድጋሜ ደስታ ዮሀንስ ያሳለፈውን ኳስ ተጠቅሞ ከአራት ጨዋታ ቅጣት የተመለሰው አምበሉ አዳነ ግርማ አስቆጥሮ ልዩነቱን አስፍቶታል።  አዳነ ግርማ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ዕድሎችን ቢያገኝም ሁለት ጊዜ የመታቸው ኳሶች በግቡ ቋሚ ተመልሰውበታል።  

የሀዋሳዎች ኃያልነት በታየባቸው ቀሪዎቹ ደቂቃዎች እስራኤል እና ፍቅረየሱስም ያደረጓቸው ሙከራዎች እንደአዳነ ሁሉ በግቡ አግዳሚ ተመልሶባቸዋል።  ሆኖም 86ኛው ደቂቃ ላይ ፍቅረየሱስ ተወልደለብርሃን የሰጠውን ኳስ እስራኤል እሸቱ አስቆጥሮ የሀዋሳን የግብ መጠን ወደ አምስት ከፍ ማድረጉ አልቀርም። ጨዋታው ተጠናቆ በተሰጠው ጭማሪ ላይ ደግሞ ተቀይሮ የገባው ወጣቱ ብሩክ በየነ ማሳረጊያዋን ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው 6-1 በሆነ ሰፊ ውጤት በሀዋሳ አሸናፊነት ተደምድሟል፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የሽረ አሰልጣኞች እና ተጫዋቾች ዳኛው ላይ  ከፍተኛ ተቃውሞ ያሰሙ ሲሆን ለጥል ሲጋበዙም ተመልክተናል፡፡