የአሰልጣኞች አስተያየት | ያገኘነውን ዕድል በመጠቀማችን እንጂ ደቡብ ፖሊስ የዋዛ ቡድን አልነበረም  ” ጳውሎስ ጌታቸው

በኢትዮጵያያ ፕሪምየር ሊግ 7ኛ ሳምንት ሀዋሳ ላይ ደቡብ ፖሊስ በባህርዳር ከተማ 1-0 ከተሸነፈበት ጨዋታ በኃላ የሁለቱ ክለቦች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን እንዲህ ሰጥተውናል። 

ያገኘነውን ዕድል በመጠቀማችን እንጂ ደቡብ ፖሊስ የዋዛ ቡድን አልነበረም  ” ጳውሎስ ጌታቸው ባህርዳር ከተማ 

ስለ ጨዋታው

“ጨዋታው በጣም ከባድ ነበር። አንደኛ ከባድ ያደረገው የአየር ንብረት ሁኔታው ነበር። እንዳያችሁት በ8 ሰዓት ነው የተጫወትነው። እንደገና ሰው ሰራሽ በሆነ ሜዳ ላይ ነበር የተጫወትነው። በጣም ሜዳው ያቃጥል ነበር። በጣም በጣም ብዙ ጉልበት አውጥተናል። ተጫዋቾቻችንን ብዙ ደክመዋል። ያገኝነውን በመጠቀማችን እንጂ ደቡብ ፖሊስ የዋዛ ቡድን አልነበረም። በጣም ብዙ ኳሶችን ስተናል። ያገኝነውን አጋጣሚ ግን ተጠቅመን ሦስት ነጥብ ይዘን በመውጣታችን ለኔ በጣም ደስታ ነው።”

ከአስናቀ ሞገስ ጋር ስለነበረው ንግግር

” የጠራሁበት የተለየ ምክንያት ምንም ነገር የለውም። በጊዜው ለግርማ እና ለአስናቀ የሰጠኋቸውን ስላልተወጡልኝ ነው ስናገረው የነበረው። የኔ ጩኸት ደግሞ ሙሉ ሜዳውን ስለሚሰማ ተጫዋቾቼ የኔን ድምፅ ከማንም ለይተው ስለሚሰሙኝ ነበር  አስናቀን አጥቅተን መጫወት ስላለብን ጉድለቱን ስነግረው የነበረው፡፡”

” የአጨራረስ ችግር ዋጋ አስከፍሎናል ” ያለው ተመስገን – ደቡብ ፖሊስ ረዳት አሰልጣኝ

ስለጨዋታው…

” በጨዋታ እንቅስቃሴ ከሌላው ጊዜ የተሻልን ነበርን። ነገር ግን ያገኘናቸውን አጋጣሚዎች መጠቀም ባለመቻላችን  የራሳችን የአጨራረስ ችግር በጣም ዋጋ አስከፍሎናል።  አሸንፈን መውጣት የምንችልባቸው ዕድሎች ፈጥረን ነበር። ነገር ግን የግብ ዕድሎችን ፈጠርን እንጂ ግብ ማግኝት አልቻልንም። ይህም እንድንሸነፍ ዋና ምክንያት ሆኗል።”