ሪፖርት | የጅማ አባጅፋር የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ጉዞ ተገቷል

በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካፈለው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊው ጅማ አባ ጅፋር በመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ በ8 ጊዜ የአፍሪካ ቻምፒዮኖቹ አል አህሊዎች በደርሶ መልስ የ2-1 ሽንፈት ከውድድሩ ውጪ ሆኗል።

በመጀመሪያው ጨዋታ ከበርካታ እንግልቶች በኃላ በጨዋታው ቀን ወደ ግብፅ አሌክሳንድርያ አቅንተው 2-0 ተሸንፈው የተመለሱት አባ ጅፋሮች በዛሬው የመልስ ጨዋታ ዲዲየ ሌብሪ በመጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ላይ ባስቆጠራት አንድ ግብ የማለፍ ተስፋቸው ቢለመልምም በሁለተኛው አጋማሽ ተጨማሪ ግብ ማከል ባለመቻላቸው የመጀመሪያው የቻምፒየንስ ሊግ ተሳትፏቸው በአሳዛኝ መልኩ ሊቋጭ ችሏል፡፡

አህሊዎች ኢላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራ ማድረግ ባልቻሉበት የመጀመሪያው አጋማሽ ጅማዎች በቀጥተኛ አጨዋወት እንዲሁም አልፎ አልፎ መሀል ለመሀል በሚደረጉ ቅብብሎች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል፡፡ በ3ኛው ደቂቃ ጅማዎች ያሻሙትን የማዕዘን ምት አህሊዎች በመልሶ ማጥቃት ወደ ጅማ የግብ ክልል ይዘው ሄደው አህመድ ኤልጋብር ከሳጥን ውጪ የሞከረው ኳስ ወደ ውጪ የወጣበት የጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራ ነበር፡፡

አህሊዎች ጥሩ ጥሩ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን ቢያገኙም ወደ ግብ የሚያደርጓቸው ሙከራዎች ኢላማቸውን የጠበቁ አልነበሩም፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ ደቂቃዎች እየገፉ ሲሄዱ ጅማዎች ይበልጥ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር በመያዝ ተጭኖ ለመጫወት ሲሞክሩ በአንጻሩ አል አህሊዎችም በብዛት በራሳቸው የሜዳ አጋማሽ ላይ በመቆየት የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን ብቻ ሲጠባበቁ ተስተውሏል፡፡ በ13ኛው በጅማዎች በኩል ዲዲዬ ለብሪ ያሻማውን ኳስ የቀኝ መስመር ተከላካዩ ከሪም ሀሰን ለመውጣት ብሎ የጨረፈውን ቢስማርክ አፒያ ወደ ግብ ሞክሮ ግብ ጠባቂው ያዳነበት ኳስ በጅማዎች በኩል የተደረገች የመጀመሪያ ጥሩ ሙከራ ነበረች፡፡

ጫና መፍጠራቸውን አጠናክረው የቀጠሉት ጅማዎች በዲዲየ ለብሪና ሄኖክ ገምተሳ ጥሩ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል፡፡ነገር ግን የመጀመሪያ አጋማሽ ተጠናቆ በተሰተጠው ተጨማሪ ደቂቃ ላይ ኤልያስ አታሮ ከግራ መስመር ያሻማውን ኳስ የመሀል ተከላካዩ መሀመድ ሀኒ በግንባሩ ለማራቅ ሲሞክር አስቻለው አግኝቶ ለዲዲዬ ለብሪ ሰጥቶት ኮትዲቯራዊው የመስመር አጥቂ አጋጣሚውን ወደ ግብነት ቀይሯት በአባ ጅፋሮች የማለፍ ተስፋን ያለመለመች የምትመስል ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡

በጅማ አባ ጅፋሮች የ1-0 መሪነት ከእረፍት የተመለሱት ሁለት ቡድኖች የቀጠልት ጨዋታ ከመጀመሪያው አጋማሽ ቀዝቀዝ ያለ እንቅስቃሴ የታየበት ነበር። በ52ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ኦሊድ አዛሮ የጅማን ተከላካዮች መዘናጋት ተከትሎ ያገኘውን ኳስ ወደ ሳጥን ውስጥ ይዞ በመግባት አክርሮ ሲመታ ይሁን እንዳሻው ተደርቦ አውጥቶበታል። በ60ኛው ደቂቃ ላይ ማማዱ ሲዲቤ ከይሁን እንዳሻው የተቀበለውን ኳስ በቀጥታ ሲሞክር አል አህሊዎች የተደረቡበትን ኳስ ዲዲዬ ለብሪ እና አስቻለው ግርማ ኳሱን መልሰው ለመጠቀም ያደረጓቸውና ያልተሳኩት ሙከራዎች በጣም አስቆጪዎች ነበሩ፡፡ አል አህሊዎች እንደመጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ በመልሶ ማጥቃት ወቅት አስፈሪዎች ነበሩ። በተለይም በ64ኛው ኦሊድ አዛሮ እንዲሁም በ75ኛው ኩሊባሊ ጥሩ ጥሩ አጋጣሚዎችን አምክነዋል፡፡

የጨዋታው የመጨረሻ 20 ደቂቃዎች ሙሉ ለሙሉ በአል አህሊዎች የሜዳ አጋማሽ ቢካሄዱም የጅማዎች ጥረት ሳይሰምር ቀርቷል ፤ በተለይም በ70ኛው ደቂቃ አፒያ ወደ ግብ የሞከረውን ኳስ መሀመድ ሀኒ ተደርቦ ሲያወጣው ያገኘውን ዲዲዬ ለብሪ አስቆጠረ ተብሎ ሲጠበቅ ሙከራው ኃይል ስላልነበረው በቀላሉ በግብ ጠባቂው የተያዘበት ሙከራ እጅግ የምያስቆጭ ነበር። በቀሩት ደቂቃዎች ጅማ አባ ጅፋሮች የተቻላቸውን ጥረት ቢያደርጉም ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ጨዋታው በጅማ የ1-0 አሸናፊነት ቢጠናቀቅም በድምር ውጤት 2-1 በሆነ ውጤት ቀጣዩን ዙር መቀላቀል ሳይችሉ ቀርተዋል ፤ በቀጣይም ቡድኑ በአፍሪካ ኮፌዴሬሽን ካፕ ተካፋይ ይሆናል፡፡