ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ኢትዮጵያ ቡና ከ ወልዋሎ ዓ/ዩ

ነገ በአዲስ አበባ ስታድየም ኢትዮጵያ ቡና ወልዋሎን በሚያስተናግድበት የፕሪምየር ሊጉ ተስተካካይ ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።

ከሦስተኛ ሳምንት መርሀ ግብሮች መካከል አንዱ የነበረው የኢትዮጵያ ቡና እና ወልዋሎ ዓ.ዩ ጨዋታ የቡና ደጋፊዎች ከአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጅነር) ጋር ወደ ባህር ዳር ተጉዘው የነበረ በመሆኑ የተላለፈ ነው። በጊዜው ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎችን አሸንፎ ሊጉን መምራት ጀምሮ የነበረው ኢትዮጵያ ቡና በቀጣይ ሳምንታት በዛው ፍጥነት መቀጠል ባይችልም ሳምንት አዳማ ከተማን በመጨረሻ ደቂቃ መርታት ችሎ ለነገው ጨዋታ ደርሷል። በተቃራኒው በተከታታይ ሽንፈቶች የሊግ ጉዞውን ጀምሮ የነበረው ወልዋሎ ይህ ጨዋታ ከተላለፈ በኋላ ካደረጋቸው ጨዋታዎች ነው አሁን አምስተኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ ያስቻሉትን ነጥቦች መሰብሰብ የቻለው። በመሆኑም ሰባተኛ ጨዋታቸውን ለማድረግ የሚገናኙት ሁለቱ ክለቦች ተስተካካይ ጨዋታዎች የሚቀሯቸው ሌሎች ክለቦች በሚሰበስቧቸው ነጥቦች ካሉበት የሦስተኛ እና አምስተኛ ደረጃ እንዳያልፏቸው ለማድረግ እንዲሁም ይበልጥ ወደ ላይ ከፍ ለማለት የሚያገኙት የመጨረሻ ዕድል ይሆናል።

ኢትዮጵያ ቡናዎች ቀዶ ጥገና ያደረገው አስራት ቱንጆ እና ኃይሌ ገብረትንሳይን በጉዳት ሳቢያ ለነገው ጨዋታ የማይጠቀሙ ሲሆን የወልዋሎዎቹ
ዳንኤል አድሓኖም ፣ ዋለልኝ ገብሬ እና ኤፍሬም ኃይለማርያምም ባለማገገማቸው ለጨዋታው የማይደርሱ ይሆናል።

ኢትዮጵያ ቡና ለነገው ፍልሚያ ከአዳማው ድል የሚያተርፈው ትልቁ ነገር የአዕምሮ ነፃነት ነው። በመሆኑም በነገው ጨዋታ ከሳምንቱ የተሻለ መረጋጋት የሚታይበት እና በቅብብሎቹ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ተፈላጊው ትዕግስት ያለው ቡድን ይጠበቃል። ቡድኑ ወደ 4-4-2 ዳይመንድ አሰላለፍ ከመጣ በኋላ አሁንም የሚያደርጋቸው የሚና ለውጦችም የጨዋታው አካል የመሆን ዕድላቸው የሰፋ ነው። ነገር ግን የካሉሻ አልሀሰን ሰፊ ሜዳ የመሸፈን ድርሻ እንደሚቀጥል ሲጠብቅ የወልዋሎ አማካዮች የጋናዊውን አማካይ እንቅስቃሴ ለመግታት ትልቅ የቤት ስራ ይጠብቃቸዋል። በወልዋሎ በኩል እንደ መከላከያው ጨዋታ ሁሉ በዋነኝነት በድንገተኛ ጥቃት ከቡና ተከላካዮች ጀርባ ለመግባት እንደሚጥር ይታሰባል። በዚህ ሂደት ውስጥ ቡድኑን በሁለት ጨዋታዎች መታደግ የቻለው አፈወርቅ ኃይሉ ሚናው ላቅ ያለ ነው። በአዳማው ጨዋታ በተደጋጋሚ ጫና ውስጥ ሲገባ የታየው የቡና የኋላ ክፍልም ከወልዋሎ ሦስት የፊት አጥቂዎች በሚሰነዘርበት ተመሳሳይ ጫና እንዳይፈተን ያሰጋዋል።

የእርስ በርስ ግንኙነቶች እና እውነታዎች

– አምና ሁለቱ ቡድኖች ለመጀመሪያ ጊዜ በተገናኙባቸው ጨዋታዎች አንድ አንድ ጊዜ አሸንፈዋል። በድምሩ ከተቆጠሩት አራት ግቦችም ውስጥ ሁለቱ የቡና ሁለቱ ደግሞ የወልዋሎ ናቸው።

– በሁለተኛው ዙር አዲስ አበባ ስታድየም ላይ በተገናኙበት ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ከ87ኛው ደቂቃ በኋላ ባስቆጠራቸው ሁለት ግቦች 2-1 አሸንፏል።

– ኢትዮጵያ ቡና አዲስ አበባ ላይ ሦስት የክልል ቡድኖችን ሲያስተናግድ ሁለቱን አሸንፎ አንድ ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።

– ወልዋሎ ዓ.ዩ እስካሁን ሦስት ጊዜ ከሜዳው ውጪ ሲወጣ ሁለቱን በ1-0 ውጤት ያሸነፈ ሲሆን በመጀመሪያው ጨዋታ ግን በሀዋሳ ከተማ የ 3-0 ሽንፈት ገጥሞት ነበር።

ዳኛ

– ፌደራል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት ይመራዋል። ጨዋታው ለአሸብር የዓመቱ ሦስተኛ ጨዋታም ይሆናል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ኢትዮጵያ ቡና (4-4-2 ዳይመንድ)

ዋቴንጋ ኢስማ

አህመድ ረሺድ – ተመስገን ካስትሮ – ክሪዝስቶም ንታምቢ – ተካልኝ ደጀኔ

አማኑኤል ዮሀንስ

ሳምሶን ጥላሁን – ዳንኤል ደምሴ

ካሉሻ አልሀሰን

ሱለይማን ሎክዋ – አቡበከር ነስሩ

ወልዋሎ ዓ.ዩ (4-3-3)

አብዱልዓዚዝ ኬይታ

እንየው ካሳሁን – ደስታ ደሙ – ቢኒያም ሲራጅ – ብርሀኑ ቦጋለ

አማኑኤል ጎበና – አስራት መገርሳ – አፈወርቅ ኃይሉ

አብዱርሀማን ፉሴይኒ – ሪችሞንድ ኦዶንጎ – ኤፍሬም አሻሞ