የአሰልጣኞች አስተያየት – “ከዚህ የተሻለ መስራት እንደምንችል ባምንም በዛሬው ውጤት ረክቻለሁ”

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሦስተኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ወልዋሎን አስተናግዶ 1-0 ካሸነፈበት ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች አስተያየት ሰጥተዋል። 
ዲዲዬ ጎሜስ – ኢትዮጵያ ቡና

“ጥሩ የሚባል ድል አስመዝግበናል። የመጀመሪያውን አጋማሽ ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር ችለናል፤ ቢሆንም በርካታ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን አምክነናል፡፡ ለወደፊቱ ከዚህ በላይ አጨራረሳችንን ማሻሻል ይኖርብናል። የተገኙ እድሎችን ተጠቅመን ቢሆን ኖሮ ጨዋታውን ያቀሉልን ነበር፡፡ 

” ጨዋታው ከሚኪ ጉዳት በኃላ በመጠኑ ተቀይሮ ነበር። እኔ ቡድኑን ማሰልጠን ከጀመርኩ ጀምሮ ሚኪያስ ምርጥ የሚባለውን እንቅስቃሴ አሳይቷል ፤ እንደ ፈጣሪ አማካይ ሳይሆን በነፃ ሚና የተሻለ መንቀሳቀስ ችሏል፡፡ ከዚህ የተሻለ መስራት እንደምንችል ባምንንም በዛሬው ውጤት ረክቻለሁ፡፡”

“የተሰጠብን የፍፁም ቅጣት ምት በእኔ በኩል ምንም ተቀባይነት የለውም፡፡”- ጸጋዬ ኪዳነማርያም- ወልዋሎ

ስለ ጨዋታው

“ሁለት በተቀራራቢ ነጥብ ላይ የነበሩ ቡድኖች እንደመገናኘታችን ለጨዋታው ትኩረት ሰጥተን ነበር የገባነው፡፡ ሜዳ ላይ ያየነው እንቅስቃሴ ብዙም የሚያስከፋ አልነበረም። ኳስ ስናጣ የነበረን የታክቲክ አተገባበር ጥሩ ነበር፤ ነገርግን ኳስ ስንይዝ ግን ትንሽ ክፍተቶች ነበሩብን፡፡ተጋጣሚያችን በሜዳው እንደመጫወቱና ዘጠና ደቂቃ መጫወት የሚችሉ ተጫዋቾችን እንደመያዙ በውጤቱ ብዙ አልተከፋሁም፡፡ የተሰጠብን የፍፁም ቅጣት ምት ግን በእኔ በኩል ምንም ተቀባይነት የለውም። ከዚህ በተሻለ እኛ ያገኘናቸው አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡”

ስለተጫዋቾች ጉዳት

“በጉዳት ያልተሰለፉ ተጫዋቾች አሉ። አንደነ አስራት መገርሳ አይነት ተጫዋቾች ደግም ከ45 ቀናት ያክል ቀናት ከእንቅስቃሴ ርቀው የነበሩ ተጫዋቾች ናቸው፡፡ ቡድናችን የጥልቀት ችግር አለበት። የእነ ዋለልኝ ገብሬ አይነት ፈጣሪ አማካዮች አለመኖርና የአጥቂያችን ዳዊት ፍቃዱ ሙሉ ለሙሉ ለጨዋታ ዝግጁ አለመሆን ችግር ፈጥሮብናል፡፡”