ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ጅማ አባ ጅፋር

ዛሬ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ የሚደረገው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ጅማ አባ ጅፋር ብቸኛ ተስተካካይ ጨዋታ ላይ ቀጣዮቹን ነጥቦች አንስተናል።

አምና እስከመጨረሻው ሳምንት በሻምፒዮንነት ትንቅንቅ ውስጥ የቆዩት ጊዮርጊስ እና ጅማ ሦስተኛ ሳምንት ላይ ይገናኙበት የነበረው ጨዋታ በብሔራዊ ቡድኑ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ምክንያት በይደር ይተያዘ ነበር። የ2010 በውጥረት የተሞላው የሁለቱ ቡድኖች ፉክክር ጨዋታውን ከወዲሁ ተጠባቂ አድርጎታል። ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች ያለግብ የጨረሱት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ስድስተኛ ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ቢሆንም የወትሮው አቋማሸው አብሯቸው አይደለም። ከአምስት ጨዋታዎች አምስት ነጥቦችን ብቻ ይዘውም አስረኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። አል አህሊን አዲስ አበባ ላይ ቢረቱም ከቻምፒዮንስ ሊጉ የወጡት ጅማዎች አሁን ፊታቸውን ወደ ሊጉ የሚያዞሩበት ሰዓት ነው። ሁለት ጨዋታዎችን ብቻ አድርገው አራት ነጥቦችን የሰበሰቡት ቻምፒዮኖቹ በተስተካካይ ጨዋታዎቻቸው ጥሩ አቋም ካሳዩ ሊጉን እስከመምራት የሚያደርስ ዕድል ይጠብቃቸዋል።

በጨዋታው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጉዳት ላይ የነበሩ ተጫዋቾቹን አገልግሎት አሁንም የማያገኝ ይሆናል። ጌታነህ ከበደ ፣ ምንተስኖት አዳነ እና መሀሪ መና መጠነኛ ልምምድ ቢጀምሩም የማይደርሱ ሲሆን አሜ መሀመድም አለማገገሙ ታውቋል። ሙሉ ስብስባቸው ለጨዋታው ዝግጁ የሆነላቸው ጅማዎች በኩል ደግሞ ዘሪሁን ታደለ ከጉዳት የሚመለስ ይሆናል።

ጨዋታው በዋነኝነት ከመስመር የሚነሱ ጥቃቶች የሚበራከቱበት እንደሚሆን ይጠበቃል። አጥቂዎቻቸውን በጉዳት ያጡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከሽረው ጨዋታ በኋላ ግብ ማስቆጠር ከብዷቸው እየታየ ነው። በስቴዋርት ሀል ስር እያየነው የሚገኘው የጊዮርጊስ የማጥቃት አማራጭ በዋነኝነት ከሁለቱ የመስመር ተመላላሾቹ እንቅስቃሴ ጋር የተቆራኘ ነው። ሆኖም ተጋጣሚዎቹ የሜዳውን የጎን ስፋት በአግባቡ ሲከላከሉ የጥቃት አቅሙ ሲዳከም ይታያል። ዛሬም  ቡድኑ ዕድሎችን በተመሳሳይ መንገድ ለመፍጠር መሞከሩ የሚቀር ባይሆንም አሁን ላይ የመሰለፍ ዕድል እያገኙ ያሉት አጥቂዎች የአጨራረስ ብቃታቸው በእጅጉ መስተካከል ይጠበቅበታል። 

የተከላካይ መስመራቸውን በተለይም በግራ እና በቀኝ በማጥቃቱ ላይ እምብዛም እንደማያሳትፉ የሚገመቱት ጅማዎችም እንደተጋጣሚያቸው ሁሉ የመስመር ጥቃትን ምርጫቸው የሚያደርጉ ይመስላል። ሆኖም ማማዱ ሲዲቤ በአል አህሊው ጨዋታ ተቀይሮ በመግባት ካሳየው እንቅስቃሴ በመነሳት ከፊት አጥቂነት ይልቅ ከአጥቂዎቹ ጀርባ ባለው ቦታ ላይ የሚንቀሳቀስ ከሆነ አባ ጅፋሮች መሀል ለመሀል ዕድሎችን የሚፈጥሩበትም አጋጣሚ መኖሩ አይቀርም። ነገር ግን ከመልሶ ማጥቃት በሚገኙ አጋጣሚዎች በፈጣን ሽግግር በዲዲዬ ለብሪ እና አስቻለው ግርማ ወይንም ኤርሚያስ ኃይሉ በኩሉ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የግብ ክልል ለመግባት እንደሚጥሩ ይታሰባል።

የእርስ በርስ ግንኙነቶች እና እውነታዎች

– አምና በጅማ አባ ጅፋር የመጀመሪያ የፕሪምየር ሊግ ተሳትፎ በቅድሚያ አዲስ አበባ ላይ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 3-0 ሲያሸንፍ የጅማው ጨዋታ ደግሞ 1-1 ተጠናቋል።

– ቅዱስ ጊዮርጊስ እስካሁን በሜዳው ካደረጋቸው ሦስት ጨዋታዎች አንድ ድል አንድ ሽንፈት እና አንድ የአቻ ውጤት አስመዝግቧል። 

– ጅማ አባ ጅፋር እስካሁን ሜዳው ላይ ጨዋታ ያላደረገ ሲሆን ዛሬ ሦስተኛ ተከታታይ የሜዳ ውጪ ጨዋታውን ያከናውናል።

ዳኛ

– ኢንተርናሽናል ዳኛ ብሩክ የማነብርሀን ከአስመራው  የኤርትራ እና የሱዳን ከ20 ዓመት ብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ መልስ ወደ ፕሪምየር ሊጉ የሚመለሰው በዚህ ጨዋታ ይሆናል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ (3-4-3)

ፓትሪክ ማታሲ

አስቻለው ታመነ – ሳልሀዲን ባርጌቾ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ 

አብዱልከሪም መሐመድ – ሙሉዓለም መስፍን – ናትናኤል ዘለቀ– ኄኖክ አዱኛ

በኃይሉ አሰፋ  – አቤል ያለው – አቡበከር ሳኒ

ጅማ አባ ጅፋር (4-3-3)                       

ዳንኤል አጄዬ

ዐወት ገብረሚካኤል – ከድር ኸይረዲን – አዳማ ሲሶኮ – ኤልያስ አታሮ

ኄኖክ ገምቴሳ – ይሁን እንዳሻው – መስዑድ መሀመድ

ዲዲዬ ለብሪ – ማማዱ ሲዲቤ – አስቻለው ግርማ