ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | በአአ ስታድየም ጨዋታዎች ንግድ ባንክ እና አአ ከተማ አሸንፈዋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዝዮን 6ኛ ሳምንት አምስት ጨዋታዎች ዛሬ ሲከሌዱ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና አዲስ አበባ ከተማ ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል። 

09:00 የጀመረው የአአ ከተማ እና ኤሌክትሪክ ጨዋታ አአ ከተማ ከመመራት ተነስቶ 2-1 አሸንፏል። በአሰልጣኝ ኢየሩሳሌም ነጋሽ የሚመሩት ኢትዮ ኤሌትሪኮች በተከታታይ ጨዋታ ነጥብ ከጣሉበት ድክመታቸው አሁንም አለመስተካከላቸው ዋጋ እያስከፈላቸው ይገኛል። ኳስ ተቆጣጥሮ በመጫወት ከተጋጣሚያቸው ብልጫ የተሻሉ ቢሆንም የጎል እድል መፍጠር እና ጎል የማስቆጠር ችግርም ዛሬ ከአዲስ አበባ ጋር ባደረጉት ጨዋታ ተስተውሏል። የግቡ ሙከራ በማድረግ ቀዳሚ የነበሩት ኤሌክትሪኮች ሲሆኑ በ12ኛው ደቂቃ አጥቂዋ ወርቅነሽ ከቅጣት ምት የመታችው በግቡ አግዳሚ ለጥቂት የወጣባት ሲጠቀስ ብዙም ሳይቆይ በ14ኛው ደቂቃ ብልጫ በመሣይ ተመስገን አማካኝነት ባስቆጠሩት የቅጣት ምት ጎል ቀዳሚ መሆን ችለዋል። 

አሰልጣኝ መሰረት ማኒ ከዚህ ቀደም በነበሩት ጨዋታዎች በመጀመርያ አሰላለፍ ከምትጠቀምባቸው አብዛኛዎቹን በተጠባባቂ ወንበር ላይ አሳርፋ በገባችበት በዚህ ጨዋታ ጠንካራ የጎል ሙከራ ባያደርጉም ወደ ጨዋታው ለመመለስ ያደረጉት ጥረት ተሳክቶላቸው በ36ኛው ደቂቃ እታፈራው አድርሴ በግንባር ገጭታ ጎል አስቆጥራ አዲስ አበባዎችን አቻ ማድረግ ችላለች። 

ከእረፍት መልስ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ በሁለቱም ቡድኖች ብንመለከትም በመሐል ሜዳ ከሚደረግ የኳስ ቅብብል ውጭ ወደ ፊት የሚሄድ ኳስ እምብዛም ባለመኖሩ ጎሎች በሁለቱም በኩል ሳይቆጠር ረጅም ሰዓት መጠበቅ አስፈልጓል። 84ኛው ደቂቃ ግን ኢትዮ ኤሌትሪኮች ግልፅ ጎል ቢያስቆጥሩም በጨዋታው ላይ ተደጋጋሚ ስህተት ትሰራ የነበረው ኢንተርናሽናል ዳኛ ፀሐይ ጎሉን ከጨዋታ ውጭ ነው ብላ መሻሯ የኤሌክትሪክ ተጫዋቾችን እና አባላትን አስቆጥቷል። አዲስ አበባዎች ወደ ጨዋታው መገባደጃ አካባቢ ያደረጉት የተጫዋች ለውጥ ተሳክቶላቸው ተቀይራ የገባችው የቀድሞዋ የደደቢት አጥቂ ቤዛ ታደሰ በ86ኛው ደቂቃ የግል ብቃቷን ተጠቅማ በግሩም አጨራረስ ጎል አስቆጥራ አዲስ አበባዎች ወሳኝ ሦስት ነጥብ እንዲያገኙ በማድረግ ጨዋታው በአዲስ አበባ 2-1 አሸናፊነት እንዲጠናቀቅ ሆናል።

እጅግ ተጠባቂው እና በርካታ የስፖርት ቤተሰብ በተከታተለው ሁለተኛው የ11:00 ጨዋታ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የመከላከያ መካከል  ተከናውኖ ንግድ ባንክ 1-0 አሸንፏል። በጣም ተመጣጣኝ እና ሳቢ በነበረው በዚህ ጨዋታ 7ኛው ደቂቃ ላይ ሽታዬ ሲሳይ ከመስመር የተሻገረላትን  ከተከላካዮች ሲደራረቡ ያገኘቸውን ኳስ ወደ ጎል መታ ለጥቂት የወጣባት፤ መከላካያዎች በአፀፋው በ9ኛው ደቂቃ ከመዲና ዐወል ተቀብላ የምስራች ላቀው ወደ ጎልነት ቀየረችው ሲባል በግቡ አናት የወጣው በመጀመርያው አጋማሽ ከተመለከትናቸው ጥሩ ሙከራዎች ዋንኞቹ ነበሩ። 

ጨዋታው እየተጋጋለ ቀጥሎ በመልሶ ማጥቃት በፈጣን እንቅስቃሴ ወደ ጎል በመቅረብ ከመከላከያዎች የተሻሉ የነበሩት ንግድ ባንኮች በ23ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት የተሻገረውን ገነሜ ወርቁ ሞክራው የወጣባት፤ በመከላከያ በኩል አልፎ አልፎ ወደ ጎል ለመድረስ በሚደረግ ጥረት ውስጥ  36ኛው ደቂቃ መዲና ዐወል በጥሩ መንገድ ለብሩክታይት አምስት ከሃምሳ ውስጥ አቀብላት ኳሱን በሚገባ ባለመቆጣጠሯ ምክንያት ተከላካዮች በፍጥነት ደርሰው ያወጡባት ጎል መሆን የሚችል የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር።

ጠንካራ ፉክክር እየተደረገበት በቀጠለው የሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታ በ56ኛው ደቂቃ ከሳጥን ውጭ ሽታዬ ሲሳይ ከቅጣት ምት የመታችው ጠንካራ ኳስ የመከላከያዋ ግብ ጠባቂ ማርታ ስትተፋው ከቅርበት የነበረችው ተከላከይዋ ገነሜ ወርቁ በግንባሯ በመግጨት ንግድ ባንኮችን ቀዳሚ እንዲሆኑ አስችላለች። 

የመከላከያ አሰልጣኝ ምንያምር በፍጥነት ከወጣቶች አካዳሚ የመጡት አረጋሽ ከልሳ እና ሲሳይ ገብረዋህድን  ቀይረው በማስገባት በተሻለ ተጭነው እየተጫወቱ ባለበት ቅፅበት የንግድ ባንኳ ብዙነሽ ሲሳይ ከዳኛዋ ጋር በፈጠረችው ሰጣ ገባ በቀይ ካርድ ከሜዳ መውጣቷ የበለጠ መከላካዮችን ብልጫ እንዲወስዱ ቢያደርጋቸውም አሰልጣኝ ብርሃኑ አጥቂዋ ሽታዬን ሲሳይን በተከላካያዋ ዘቢብ ኃይለሥላሴ በመቀየር ውጤቱን ለማስጠበቅ ወደ ኋላ በማፈግፈግ የቀረውን ደቂቃ ጨርሰዋል። የቁጥርም የእንቅስቃሴም ብልጫ የወሰዱት መከላከያዎች ቀሪውን ደቂቃ ጠንካራውን የንግድ ባንክ ተከላካዮችን አልፈው ጎል ማስቆጠር ሳይችሉ በመቅረት ተጠባቂው ጨዋታ በንግድ ባንክ 1-0 በሆነ ጠባብ ውጤት አሸናፊነት ተጠናቋል።