የአሰልጣኞች አስተያየት | ቅዱስ ጊዮርጊስ 0-0 ኢትዮጵያ ቡና

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ስምንተኛ ሳምንት ተጠባቂው የሸገር ደርቢ 0ለ0 በሆነ ውጤት ከተጠናቀቀ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

“በጨዋታው ዳኛው የወሰነው ብቸኛ ትክክለኛ ውሳኔ ቀይ ካርዱ ብቻ ነው” ስቴዋርት ሃል – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ስለ ጨዋታው

“በመጀመሪያዎቹ 25 ደቂቃዎች ጥሩ መንቀሳቀስ ችለናል። ከዛም በፈጠርናቸው ክፍተቶች ወደ ጨዋታው እንዲመለሱ ፈቅደንላቸው ነበር፡፡ መሀል ሜዳ ላይ ከኛ በተሻለ የአንድ ሰው የቁጥር የበላይነት ስለነበራቸው በተወሰነ መልኩ ችግሮችን ሲፈጥሩብን ስለነበር በእረፍት ሰዓት ከተጫዋቾቼ ጋር ተነጋግረን ይህን ለማሻሻል ሞክረን ነበር። ነገርግን ቀይ ካርዱ ሁሉንም ነገር ነው የቀየረብን፡፡ ተጫዋቾቼ በነበራቸው የመንፈስ ጥንካሬ በጎዶሎ ተጫዋች ሳንሸነፍ ልንወጣ ችለናል፡፡”

ስለ ዳኝነቱ

” በጨዋታው ዳኛው የወሰነው ብቸኛ ትክክለኛ ውሳኔ ቢኖር ቀይ ካርዱ ብቻ ነው፤ ቀይ ካርዱ ፍፁም ትክክል ነበር። ከዛ ውጭ የነበሩት ውሳኔዎቹ በሙሉ እጅግ የተሳሳቱ ነበሩ። የዳኛው ውሳኔዎች በጣም አሰቃቂ ነበሩ፡፡”

ስለ አጠቃላይ የቡድኑ ማጥቃት ሂደት

” መስራት ያሉብን ነገሮች እንዳሉ አምናለው፤ ጌታነህ ከበደና ሰልሀዲን ሰዒድ አሁንም ቢሆን ሙሉ ለሙሉ ለጨዋታ ዝግጁ አይደሉም። ሁለቱንም ለጨዋታ ዝግጁ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ ያንን ማድረግ ከቻልን የሊጉን አስፈሪ ጥምረት መፍጠር እንችላለን፡፡ በጎዶሎ ተጫዋች ለመጫወት ብንገደድም አጥቂ አስወጥተን በምትኩ ያስገባነው የአጥቂ ስፍራ ተጫዋች ነው። እንደ አጠቃላይ አሉታዊ አቀራረብ አልነበረንም፡፡”

ስለ ዋንጫ ፉክክሩ

“አሁንም ቢሆን የዋንጫ ፉክክር ውስጥ ነው የምንገኘው ፤ በየትኛውም ሀገር ዋንጫ አሸናፊው ከገና በፊት አይለይም፡፡ ከኃላ ጀምረን ቡድናችንን እየገነባን እንገኛለን ፤ አሁን በመከላከሉ ረገድ ጥሩ ነበርን አሁን በቀጣይ መስራት የሚጠበቅብን ከጎል ፊት የሚቀሩን ስራዎች ላይ ጠንክረን መስራት ይኖርብናል፡፡ ”


የቁጥር ብልጫውን ባለመጠቀማችን በመጠኑም ቢሆን ተከፍተናል”- ዲዲዬ ጎሜስ – ኢትዮጵያ ቡና

ስለ ጨዋታው

“በውጤቱ በመጠኑም ቢሆን ተከፍተናል። ምክንያቱም በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለት ግብ ልናገኝባቸው የምንችልባቸውን አጋጣሚዎችን አምክነናል፡፡ በዛሬው ጨዋታ በተጫዋቾቼ እጅጉን ኮርቻለሁ፤ ልነግራቸው የምፈልገው ነገር ቢኖር በጣም እንደምወዳቸው ነው። ምክንያቱም በዛሬው ጨዋታ በአዲስ አሰላለፍ እንድንጫወት ያቀረብኩላቸውን ሀሳብ ተቀብለው በ6 አማካይ ተጫዋቾች እንድንጫወት በነገርኳቸው መሠረት የሚችሉትን ለማድረግ ሞክረዋል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ ባቀድነው መሠረት የሚገኙትን ክፍተቶች መጠቀም አልቻልንም። በተጨማሪም በመጀመሪያው አጋማሽ ትዕግስት ተላብሰን መጫወት አልቻልንም፤ በሁለተኛው አጋማሽ ይበልጥ በአጫጭር ኳሶች መጫወት ፈልገን ነበር፡፡ በአጠቃላይ በሁለት ጥሩ ቡድኖች መካከል የተደረገ ጨዋታ እንደመሆኑ ጥሩ የሚባል ነበር፤ በጎዶሎ ተጫዋች እንደመጫወታቸው ጨዋታውን ልናሸንፍ የምንችልበትን እድል የነበረ ቢሆንም ባለመጠቀማችን በመጠኑም ቢሆን ተከፍተናል፡፡”

ስለቡድኑ የግብ ማግባት ድክመት

“ይህ ችግር እንዳለ እረዳለሁ፤ እንደምናገኛቸው አጋጣሚዎች ግብ በማስቆጠሩ ረገድ ደካማ ነን፡፡በዛሬው ጨዋታ እንደከዚህ ቀደሞቹ በርካታ የግብ እድሎችን መፍጠር ባንችልም ያገኘናቸውን ጥቂት አጋጣሚዎችን መጠቀም አልቻልንም፡፡ ችግሩ ግለሰባዊ አይደለም። በልምምድ ላይ አጥቂዎቻችን እለት ከእለት የሚያደርጉትን ጥረት ስለምመለከት ይህ ችግር የተጫዋቾቻችንን የራስ መተማመን በማሳደግ የሚፈታ ይመስለኛል፡፡”