ሪፖርት | መቐለ 70 እንደርታ ወደ አሸናፊነት የተመለሰበት ድል ሲዳማ ቡና ላይ አስመዘገበ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዘጠነኛ ሳምንት የዛሬ መርሐ ግብር ከሆኑት መካከል አንዱ የሆነው የመቐለ 70 እንደርታ እና ሲዳማ ቡና ጨዋታ በባለሜዳው መቐለ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
መቐለዎች ባሳለፍነው ሳምንት ከሽረ አቻ ከተለያየው ስብስባቸው አቼምፖንግ አሞስ እና ኦሴይ ማውሊን በማሳረፍ ሥዩም ተስፋዬ እና ሳሙኤል ሳሊሶን ተክተው ሲገቡ እንግዶቹ ሲዳማ ቡናዎች በበኩላቸው በመሣይ አያኖ፣ ጫላ ተሺታ እና ዳዊት ተፈራ ምትክ ፍቅሩ ወዴሳ፣ አበባየሁ ዮሃንስ እና ወንድሜነህ ዓይናለምን ተጠቅመዋል። 

በአወዛጋቢ ዳኝነት የታጀበው ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች በሚደርጓቸው ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴዎች የጀመረ ሲሆን በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች በርካታ የጎል ሙከራዎች አስተናግዷል። በተለይም ፍሊፕ ኦቮኖ መትቶ ከግብ ክልሉ በደምብ ያላራቀው ኳስ ተጠቅሞ ዮናታን ፍስሃ ያደረገው ሙከራ ለግብ የቀረበ ነበር። ከመጀመርያው ደቂቃ አንስቶ ለማጥቃት ከፍተኛ ፍላጎት ያሳዩት ባለሜዳዎቹ መቐለዎች በአራተኛው ደቂቃ ያገኙትን የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚ በአግባቡ ተጠቅመው መሪ መሆን ችለዋል። ሥዩም ተስፋዬ ከመስመር ያሻማውን ኳስ ያሬድ ከበደ በአግባቡ ተጠቅሞ መቐለን መሪ ማድረግ ችሏል። የሲዳማ ቡና ያልተረጋጋ የመከላከል አደረጃጀትን ተጠቅመው ተደደጋሚ ግዜ ወደ ግብ የደረሱት መቐለዎች ሁለተኛውን ጎል ለማስቆጠር ብዙ ደቂቃ አልጠበቁም። በስምንተኛው ደቂቃ አማኑኤል ገ/ሚካኤል በጥሩ ሁኔታ ይዞት የገባው ኳስ ለሳሙኤል ሳሊሶ አቀብሎት ሳሙኤል ከሳጥን ውጭ አክርሮ በማስቆጠር የመቐለን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል።

በጨዋታው ከተለጠጠው የመስመር አጨዋወቱ በተጨማሪ የአማካይ ተሰላፊዎቻቸው ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ተጠግተው እንዲጫወቱ ያደረጉት መቐለዎች በርካታ ዕድሎች ፈጥረዋል። በተለይም አማኑኤል ገ/ሚካኤል ከያሬድ ከበደ የተቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ ያደረገው ሙከራ እና ራሱ ሓይደር ሸረፋ በጥሩ ሁኔታ ያሻማው ኳስ የሲዳማ ተከላካዮች ከጨዋታ ውጭ ብለው በቆሙበት ወቅት አማኑኤል ያደረገው ሙከራ ከታዩት ሙከራዎች ይጠቀሳሉ። ኬንያዊው ሰንደይ ሙቱኩን ቀይረው ካስገቡ በኋላ የተከላካይ ክፍላቸው በመጠኑ የተረጋጋው ሲዳማ ቡናዎች በመጀመርያው አጋማሽ ንፁህ የግብ እድል ባይባሉም ጥቂት የግብ ዕድሎች ፈጥረዋል። ዮሴፍ ዮሐንስ ከርቀት መትቶ ያደረገው ሙከራ እና ወንድሜነህ ዓይናለም ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ አክርሮ መትቶ የመቐለ ተከላካዮች ተደርበው ያወጡት ይጠቀሳሉ።

ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ የፉክክር መንፈስ የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ ግብ ያስተናገደው ገና በሁለተኛው ደቂቃ ላይ ነበር። በመቐለ የግብ ክልል የተሻማ ኳስን ለማግኘት በነበረው ግርግር በተፈፀመው ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት አዲስ ግደይ በአግባቡ ተጠቅሞ ሲዳማን ወደ ጨዋታው የመለሰች ጎል አስቆጥሯል። ረዳት ዳኞች በሚወስኗቸው አወዛጋቢ ውሳኔዎች ታጅቦ በቀጠለው ጨዋታ ሲዳማ ቡናዎች ግብ ካስቆጠሩ በኋላ የተሻለ መነሳሳት ቢያሳዩም እንቅስቃሴው ለብዙ ደቂቃዎች የቆየ አልነበረም። በዚህም አዲስ ግደይ እና ጸጋዬ ባልቻ በተናጠል ከሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ውጭ እንደ ቡድን ማጥቃት አልቻሉም።

በሁለተኛው አጋማሽም ከተጋጣሚያቸው ሲዳማ በተሻለ የተጠና የማጥቃት አጨዋወት የተከተሉት መቐለዎች በርከት ያሉ የግብ አጋጣሚዎችን ማግኘት ችለዋል። ከነዚህም አማኑኤል ገ/ሚካኤል ከቅጣት ምት ሞክሮት ፍቅሩ ወዴሳ በሚያስደንቅ ብቃት ያወጣው፣ ሥዩም ተስፋዬ እና ያሬድ ከበደ በጥሩ ሁኔታ ገብተው የፈጠሩት የግብ ዕድል እና ያሬድ ከበደ በጥሩ ሁኔታ ገብቶ ፈቱዲን ጀማል ደርሶ ያስጣለው ከታዩት ሙከራዎች መካከል ይጠቀሳሉ። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾች አስገብተው የተሻለ የግብ ዕድል ፈጥረዋል። ከነዚህም የሲዳማ ቡናው ሃብታሙ ገዛኸኝ አክርሮ መቶ ፍሊፕ ኦቮኖ ያዳነው ኳስ ይጠቀሳል።

በ84ኛው ደቂቃ ተቀይሮ በመግባት ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረገው ዮናስ ገረመው በጥሩ ሁኔታ ያሻገረው ኳስ አማኑኤል ገ/ሚካኤል አግኝቶ በማስቆጠር የመቐለን መሪነት ወደ 3-1 ከፍ ማድረግ ችሏል። ጨዋታውም ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠርበት በመቐለ አሸናፊነት ተጠናቋል። የመጀመርያዎቹን ሁለት ጨዋታዎች በማሸነፍ መልካም አጀማመር አድርጎ የነበረው መቐለም ከተከታታይ አራት ድል አልባ ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት ተመልሷል። 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *