የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በሴካፋ ዋንጫ አይሳተፍም

የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ማኅበር (ሴካፋ) በዩጋንዳ አስተናጋጅነት ሊያካሂደው ባሰበው ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እንደማይካፈል ታወቀ።

ሴካፋ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫን ዘንድሮ ለ3ኛ ጊዜ በዩጋንዳ አዘጋጅነት እንደሚያካሂድ ባሳለፍነው ሳምንት የሴካፋው ዋና  ኒኮላስ ሙሶንዬ ይፋ ማድረጋቸው ይታወቃል። በውድድሩም 11 የሴካፋ አባል ሀገራት እንደሚካፈሉበት የተገለፀ ሲሆን የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድንም ይካፈላል ተብሎ ቢጠበቅም የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባደረገው መደበኛ ስብሰባ ብሔራዊ ቡድኑ እንደማይካፈል ከውሳኔ ላይ ደርሷል። ኢትዮጵያ በውድድሩ ላይ የማትሳተፈው በበጀት እጥረት እንደሆነ ለማወቅ ችለናል።

በ2006 በታንዛኒያ አዘጋጅነት ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገው የሴካፋ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ በ2010 በኤርትራ ከተሰናዳ በኋላ ላለፋት ዓመታት በተለያዩ ምክንያቶች ሳይደረግ ቆይቶ ከ8 ዓመት በኋላ ዘንድሮ ውድድሩ ዳግም ተመልሶ ይደረጋል ቢባልም የመካሄዱ ነገር አሁንም አጠራጣሪ ሆኗል። ዛንዚባር በውድድሩ ላይ እንደማትሳተፍ ከዚህ ቀደም ለሴካፋ ማረጋገጫ መስጠቷ ይታወቃል። በሌላ ዜናም የሴካፋ ከ20 ዓመት ዋንጫን ታዘጋጃለች ተብላ የተጠበቀችው ዩጋንዳ ውድድሩን እንደማታስተናግድ ለሴካፋ ማሳወቋ እየተነገረ ይገኛል።                  

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከሴካፋ ውድድር እንደማይሳተፍ በስራ አስፈፃሚ ደረጃ ከውሳኔ ይድረስ እንጂ በየካቲት ወር በአስመራ አስተናጋጅነት በሚካሄደው እና በኤርትራ፣ ኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ እና ሶማሊያ ወጣት ቡድኖች መሃከል በሚደረገው ‘የሰላም እና ወዳጅነት ዋንጫ’ ላይ ይሳተፍ አይሳተፍ እስካሁን ማረጋገጫ አልሰጠም።
በ2019 የአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ማጣርያ የመጀመርያ ዙር መጋቢት ወር ላይ በቡሩንዲ ተሸንፎ ከወደቀ በኋላ ወጣት ቡድናችን ከጨዋታ ርቋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *