ሪፖርት | ባህር ዳር ከተማ ዳግም ወደ አሸናፊነት የተመለሰበትን ድል ደደቢት ላይ አግኝቷል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 10ኛ ሳምንት አራት ጨዋታዎች በክልል እና አዲስ አበባ ሲደረጉ በግዙፉ ባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ደደቢትን የጋበዘው ባህር ዳር ከተማ 2ለ0 አሸንፏል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ጨዋታው ነገ እንደሚደረግ ቀድሞ ለሚዲያዎች በላከው መልክት ቢያሳውቅም ለውጥ ተደርጎበት ጨዋታው ዛሬ ተከናውኗል።

በአማራ እና ትግራይ ክልሎች መካከል በነበረው አለመግባባት የሁለቱ ክልል ክለቦች የሚያደርጓቸው የእርስ በእርስ ጨዋታዎች በገለልተኛ ሜዳዎች ሲደረጉ የቆዩ ሲሆን ከሳምንት በፊት ፋሲል ከነማ ወደ መቐለ አምርቶ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲን ከገጠመ በኋላ ሁለተኛ የሁለቱ ክልል ክለቦች ጨዋታ ዛሬ ባህር ዳር ላይ ተከናውኗል። በጨዋታውም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስን ጨምሮ የባህር ዳር ከተማ ከንቲባ አቶ ሙሉቀን በስታዲየሙ ሲታደሙ በመረጃ እጥረት እና በተለያዩ ምክንያቶች የክለቡ ደጋፊዎች እንደ ከዚህ ቀደሙ በሜዳ አልተገኙም።

ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት የባህር ዳር ከተማ ደጋፊዎች ማኅበር ለደደቢት እግር ኳስ ክለብ ከተማዋን የሚያስተዋውቅ ፎቶ ግራፍ በፍሬም አድርገው በስጦታነት ያበረከቱ ሲሆን ስጦታውን የደደቢት አምበል ኤፍሬም ተቀብሏል።

ባለሜዳዎቹ ባህር ዳር ከተማዎች በ9ኛ ሳምንት ወደ ድሬዳዋ አምርተው ከተሸነፉበት ስብስብ መካከል ግብ ጠባቂያቸው ምንተስኖት አሎ፣ ተስፋሁን ሸጋው፣ ኄኖክ አቻምየለህ፣ ቴዎድሮስ ሙላት፣ ዜናው ፈረደ እና ፍቃዱ ወርቁን በሀሪሰን ሄሱ፣ ሳላምላክ ተገኝ፣ ወንድሜነህ ደረጄ ፣ ፍቅረሚካኤል ዓለሙ፣ ወሰኑ አሊ እና ጃኮ አራፋት ተክተው ገብተዋል። ተጋባዦቹ ደደቢቶች ደግሞ በዓመቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ወላይታ ድቻ ላይ ድል ካገኙበት የመጀመርያ 11 እንዳለ ከበደን በዳግማዊ አባይ ብቻ በመለወጥ ለጨዋታው ቀርበዋል።

ጨዋታውን ባለሜዳዎቹ ባህር ዳሮች ብልጫ ወስደው የተንቀሳቀሱበት ሲሆን ተጋባዦቹ ደደቢቶች ደግሞ በራሳቸው ሜዳ አብዛኛውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በማሳለፍ ወደ ኋላ አፈግፍገው ተጫውተዋል። በጉዳት ምክንያት ሁለት ጨዋታዎች ያለፋቸው ጃኮ አራፋት እና ወሰኑ ዓሊ በ5፣ 10 እና 12ኛው ደቂቃ ከቆሙ ኳሶች እና ከመስመር በሚላኩ ረጃጅም ኳሶች ቡድናቸውን በጊዜ መሪ ለማድረግ ቢሞክሩም ኳሶቹ ኢላማቸውን በመሳታቸው መረብ ላይ ሳያርፉ ቀርተዋል። ከሶስቱ ሙከራዎች በተጨማሪ በ16ኛው ደቂቃ ጃኮ ኤሊያስ ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኘውን የቅጣት ምት በቀጥታ አክርሮ በመምታት ሌላ የግብ ማግባት ሙከራ ቢያደርግም ኳሱ የግቡን ቋሚ ታኮ ወደ ውጪ ወጥቷል።

ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ ወደ ደደቢቶች የግብ ክልል የደረሱት ባህር ዳሮች በወሰኑ ዓሊ አማካኝነት ጥሩ አጋጣሚ ፈጥረው መክኖባቸዋል። አሁንም ጫና ማድረጋቸውን የቀጠሉት የአሰልጣኝ ጳውሎስ ተጨዋቾች ተጭነው ተጫውተው በ27ኛው ደቂቃ የማዕዘን ምት አግኝተዋል። የማዕዘን ምቱንም ግርማ ዲሳሳ አሻምቶት የደደቢቱ አምበል ኤፍሬም ጌታቸው በራሱ መረብ ላይ በማስቆጠሩ መሪ ሆነዋል። ግብ በማስቆጠራቸው ይበልጥ የተነቃቁት ባህር ዳሮች በ29ኛው ደቂቃም በግርማ አማካኝነት መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ ሊያደርግ የሚችል አጋጣሚ አግኝተው ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል።

በአንድ አጥቂ መጫወትን የመረጡት ደደቢቶች በራሳቸው የሜዳ ክፍል ጥቅጥቅ ብለው በመከላከል ለተጋጣሚያቸው ፈተና ሆነው ለመጫወት ሞክረዋል። በዚህም የጨዋታ አቀራረብ ወደ ባህር ዳር የግብ ክልል ሄደው ሙከራዎችን ለማድረግ የተሸገሩት ደደቢቶች አኪዌር ቻሞን ኢላማ ያደረጉ ረጃጅም ኳሶቻቸው በመጣል ለመጫወት ሞክረዋል። ይሁን እና በቁጥር ብልጫ የተወሰደበት የደደቢት የአጥቂ ክፍል ከመዋለል ውጪ በመጀመሪያው አጋማሽ ምንም የግብ ማግባት ሙከራ ሳያደርግ ወደ መልበሻ ክፍል አምርቷል።

ባህር ዳሮች ከዚህ ቀደም በሜዳቸው እንደሚያደርጉት በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ተጭነው የተጫወቱ ሲሆን ሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ በአራተኛው ደቂቃ ግብ አስቆጥረው መሪነታቸውን ወደ ሁለት አሳድገዋል። ወሰኑ ላይ የተሰራውን ጥፋት በመጠቀም ወደ ደደቢቶች የግብ ክልል በቀላሉ የደረሱት ባህር ዳሮች በጃኮ አራፋት አማካኝነት ግብ አስቆጥረዋል።

ይህቺ ጎል ያነቃቸው የሚመስሉት ደደቢቶች ከ50ኛው ደቂቃ በኋላ በአንፃራዊነት ጥሩ ተንቀሳቅሰዋል። በ51ኛው ደቂቃም በጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራቸው በአለምአንተ ካሳ ጠንካራ ኳስ ግብ ለማስቆጠር ጥረው መክኖባቸዋል። ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ከቆመ ኳስ ቡድኑ ሌላ የግብ ማግባት ሙከራ አድርጎ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ቢሞክርም ሳይሳካለት ቀርቷል። መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ ካደረጉ በኋላ በአንፃራዊነት ወደ ኋላ አፈግፍገው የተጫወቱት ባህር ዳሮች ከፊታቸው ትተውት የነበረው የሜዳ ክፍል ደደቢቶች ተጠግተው በመጠቀም ጫና ለማድረግ ሞክረዋል። በ66ኛው ደቂቃ ዳግማዊ ዓባይ ከቆመ ኳስ የቡድኑን ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ያደረገ ተጨዋች ሲሆን ኳሱን ለመጀመሪያ ጊዜ የመጀመርያ ተሰላፊነት እድልን ያገኘው ሃሪሰን ሄሱ ተቆጣጥሮታል።

ጨዋታውን ለመቆጣጠር ሲሞከክሩ የነበሩት ነገር ግን ያልተሳካላቸው ባህር ዳሮች በተለይ በቀኝ መስመር ጥቃቶችን ሲያስተናግዱ ታይተዋል። በ85ኛው ደቂቃም ከቀኝ መስመር የተሻማን ኳስ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው እንዳለ ከበደ ተገልብጦ የቀድሞ ክለቡ ላይ ጎል ለማስቆጠር ቢሞክርም ሳይሳካለት ቀርቷል። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ተጠናቆ በጭማሪ ሰዓት ጃኮ በረጅሙ ከግብ ጠባቂው ጋር ያገናኘውን ኳስ ተቀብሎ ወደ ጎል የደረሰ ሲሆን ተጨዋቹ ግብ ጠባቂው ረሺድ ማታውሲን አልፌ አገባለው ብሎ ተቀምቷል። ጨዋታውም ተጨማሪ ጎል ሳያስተናግድ ተጠናቋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *