ታክቲካዊ ትንታኔ ፡ ኢትዮጵያ ቡና 1-0 ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ


ሚልኪያስ አበራ


 

 

በአምበር ዋንጫ ላይ ከፍተኛ መሻሻልን እንዳሳየ በብዙዎች ሲነገርለት የነበረው ኢትዮጵያ ቡና በአንፃሩ በርካታ የሊግ ልምድ ያላቸው ተጫዎቾች በክረምቱ የተጫዎቾች የዝውውር መስኮት ካሰባሰበው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር የዘንድሮውን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ጨዋታውን በአዲስ አበባ ስታዲየም አከናውኖ ከጨዋታ ብልጫ ጋር በመጀመሪያ ደቂቃ ላይ ያቡን ዊልያም ባስቆጠራት ጎል አሸንፏል፡፡

የመጀመርያ አሰላለፍ

በአዛውንቱ ስርቢያዊ አሰልጣኝ ድራገን ፓፓዲች የሚሰለጥነው የኢትዮጵያ ቡና በዘንድሮው አምበር ዋንጫ ያሳየውን የዳይመንድ ፎርሜሽን (4-4-2Diamond /4-1-2-1-2) የተጫዋቾች የሜዳ ላይ የቦታ አያያዝን ተመርኩዞ ጨዋታውን የጀመረ ሲሆን በቀድሞው የትራንስ ፣ ሐረር ቢራ እና ኢትዮጵያ ቡና አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም የሚመራው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደግሞ በመጀመሪያዎቹ የጨዋታው 20 ደቂቃዎች የቡድኑን መነሻ የተጫዎቾች የሜዳ ላይ አደራደርን (Formation) ለመለየት አስቸጋሪ ቢመስልም ወደ 4-1-3-2 የተጠጋ አሰላለፍን እስከ መጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍሉ ጊዜ መጠናቀቂያ ድረስ ሲጠቀም እንደነበር ተተስተውሏል፡፡

(ምስል 1)

የጥላሁን ወልዴ ሚና

በጨዋታው የኢትዮጵያ የDiamond Formation አጠቃቀም ቀልብን ያዝ የማድረግ አቅም ነበረው፡፡ በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ፡፡

የ4-1-2-1-2 የተጫዋቾች የሜዳ ላይ አደራደር ተለምዳአዊ Width (በሜዳው ቁመት የሚኖሩ ስፋትን) የማሳጣት ችግር እንዳለበት ይጠቀሳል፡፡ በዘመናዊው እግር ኳስ አሰልጣኞች ይህንን ክፍተት ለመድፈን ከሁለቱ የመሃል ተከላካዮች እና ከብቸኛው የተከላካይ አማካይ ውጪ ያሉትን ተጫቾች በሙሉ የጨዋታውን የእንቅስቃሴ ሒደት ላይ የተመሰረተ Width (ስፋት) የማበርከት ኃላፊነትን ይሰጧቸዋል፡፡

የመስመሩ ተከላካዮች ወደፊት ተደጋጋሚ የማጥቃት ሩጫ (Overlapping Run) እንዲያደርጉ በማድረግ፣ የመሃል አማካዮች (Shuttlers) እና አጥቂዎች ወደ መስመር ተጠግተው እንዲጫወቱ በማድረግ ለቡድናቸው Width ሲሰጡ ይታያል፡፡

በኢትዮጵያ ቡና የአጥቂ መስመር በግራው በኩል ተሰልፎ የነበረው የጥላሁን ወልዴ እንቅስቃሴ ቡድኑ በመስመሩ ለነበረው ታክቲካዊ የበላይነት አብይ ምክንያት ነበር፡፡ ጥላሁን ወደ መስመር እየተጠጋ እና ወደ ኃላ እየተመለሰ ከኤልያስ እና አህመድ ጋር በተደራጀ እንቅስቃሴ (Organized Movement) የቦታውን እንቅስቃሴ ሲመሩ ተሰተውሏል፡፡ በንግድ ባንኮች ላይ የቁጥር ብልጫ ለመውሰድም (Flank Over Loading) የጥላሁን ድርሻ ከፍተኛ ነበር፡፡ የኤልያስን የመከላከል ድክመት ለመሸፈን የነበረው ሚናም ተጠቃሽ ነበር፡፡ በተለይ መስመሩ ንግድ ባንኮች ባለፈው ዓመት በተለይም በመጀመሪያው የውድድር ግማሽ ዓመት ተጋጣሚ ላይ ጫና የሚያሳድሩ የማጥቃት አጨዋወት የሚመሰርተው በዚህ መስመር ከሚሰለፈው አዲሱ ሰይፉ ከመሆኑ አንፃር የሱን ሚና መገደብ እንዲችሉ እና ከፊት ለፊቱ ካለው አማካይ (ኤፍሬም አሻሞ) ጋር እንዲለያይ ያደረጉት መንገድ ጥሩ ታክቲካዊ ውሳኔ ነበር፡፡ በመጀመሪያው ደቂቃ ላይ ያስቆጠሯት ጐልም መነሻ መስመሩ ይህኛው መሆኑ ሲታይ የጥላሁን ወልዴ እገዛ ከፍተኛ ነበር፡፡

(ምስል 2)

buna 1-0 bank image 2

የቡና የመስመር ተከላካዮች እንቅስቃሴ

በጨዋታው ከታየዩት የቡና አዎንታዊ ጐኖች መካከል የመስመር ተከላካዮቹ የተጠና እንቅስቃሴ ነበር፡፡

የአህመድ ረሺድ እና አብዱልከረም መሃመድ በጨዋታው ሒደት የነበራቸው የአጨዋወት ሥርዓት ቡድኑ በአንፃራዊነት በጨዋታው ለነበረው የበላይነት ተጠቃሽ ምክንያት ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ፡፡ ሁለቱ የመስመር ተከላካዮች የነበራቸው መናበቡ እና ጨዋታውን የመረዳት ግንዛቤ ይበል የሚያስኝ ነበር፡፡

በማጥቃት የአጨዋወት ሒደት አብዱልከሪም የፊት ለፊት የማጥቃት እነቅስቃሴ (overlap) ሲያደርግ አህመድ ረሺድ ወደ ኃላ በመቅረት ሁለቱን የመሃል ተከላካዮች በመቀላቀል ግዜያዊ የሶስት ተከላካዮች ጥምረት (Back-3) በመስራት ቡድኑን ከመልሶ ማጥቃት የሚመጣን ጥቃት እንዲከላከል የሚያደርግ የመከላከል አደረጃጀት ሲፈጥሩ ነበር፡፡ ይህ የተጫዋቶቹ እንቅስቃሴ የቡድኑ የማጥቃት ኢላማን መሰረት ያደረገ መሆኑ በቀላሉ በትክክለኛው ቦታ ላይ ትክክለኛ ሰዓት ላይ እንዲገኙ ሲያስችላቸው ነበር፡፡

(ምስል 3)

buna 1-0 bank image 3

ታክቲካዊ ለውጦች ላይ የተመሰረቱ ቅያሪዎች

ንግድ ባንክ

የአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማሪያም ቡድን በጥሩ አቋም ላይ አይገኝም፡፡ በመጀመሪያዎች የጨዋታው 20 ደቂቃዎች ቅርፀ-ቢስ መስለው ታይተዋል፡፡ የተከላካይ ክፍሉ ከፍተኛ የመደራጀት እና የስራ መተማመን ችግር ይታይበታል፡፡ በተለይ የግራ መስመሩ፡፡

በመከላከል የጨዋታ ሒደት channels (በመሃል ተከላካዩ እና በመስመር ተከላካዩ መካከል ያለው ቦታ) ስፊ ሆነው ይታያሉ፡፡ የአማካዩች እንቅስቃሴም ዘፈቀዳዊ ይዘት ያለው ይመስላል፡፡ ኤፍሬም ፣ ሰለሞን እና አብዱልከሪም ሃሰን አላስፈላጊ እና ተደጋጋሚ የቦታ ለውጦችን ይከውናሉ፡፡ ቡድኑ በ12ኛ ደቂቃ በወንድይፍራው እና አብዱልከሪም(ቡና) መካከል በተደረገ ያልተሳካ የኳስ ቅብብል የተገኘችውን ኳስ ኤፍሬም ሞክሯት አግዳሚ ከመለሰበት የጐል መከራ ውጪ በአደገኛነት የሚጠቀስ ሙከራ ሳያደርግ የመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ግዜ አጠናቋል፡፡

ከዕረፍት መልስ በተደረገ የተጫዋች ለውጥ በጨዋታው የደከመ እንቅስቃሴ ያደረገው አብዱልከሪምን አስወጥተው ፍቅረየሱስን ካስገቡና አምሃ በለጠን በቢንያም ከቀየሩ በኋላ ቡድኑ ባለፈው አመት በአመዛኙ ሲጠቀምበት ወደነበረው 4-1-4-1 ተመልሷል፡፡ መጠነኛ መሻሻልን በዚህኛው የጨዋታ አጋማሽ ቢያሳዩም ተቀይረው የገቡት ተጫዋች ያን ያህል ቀድሞ ከነበሩት የተሻለ እንቅስቃሴን ማድረግ አልቻሉም፡፡ ተቀይረው የገቡት ሁለቱም ተጫዋቾች የቦታ አጠባበቅ ችግርም ተስተውሎባቸዋል፡፡

በአብዛኛው የጨዋታው ክፍለ ግዜ የአጥቂው መስመር ተነጥሎ ታይቷል፡፡ አምና በአሰልጣኝ ፀጋዬ 4-1-4-1 እና 4-2-3-1 ፎርሜሽኖች ጎልቶ የወጣውና በርካታ ግቦች ማስቆጠር የቻለው ፊሊፕ ዳውዚ ከቢንያም ጋር የተጣመረበት መንገድ ውታማ አልነበረም፡፡ ፊሊኘ ዳውዚን እና ቢንያም አስፋን የጨዋታው አካል ለማድረግ የሚያስችል ሲስተምን አስልጣኝ ፀጋዬ ገና የዘረጉ አይመስልም፡፡

ንግድ ባንክ በተጫዋቾች ዝውውር ወቅት ጥራት ካላቸውና የቡድኑን ደረጃ ከፍ ሊያደርጉ ከሚችሉ ግዢዎች ይልቅ የሚፈፅመው <<የማግበስበስ>> ሒደት ቡድኑን ብዙም የሚያሻሽለው አይደለም፡፡ አምና የአሰልጣኝ ፀጋዬን ታክቲክ በመተግበር ረገድ የተሻሉ የነበሩት ተጫዋቾች በዘንድሮ ስብስብ ቦታ አጥተዋል፡፡

ከዕረፍት መልስ አሰልጣኝ ድራገን ፓፓዲች ጥላሁን ወልዴን ወደግራ መስመር አማካይነት ፣ ኤልያስ ማሞን ደግሞ በዳይመንዱ የላይኛው ጫፍ ላይ በማሰለፍ እንዲሁም ዮሴፍ ዳሙዬን ከሁለቱ አጥቂዎች የቀኙን መስመር እንዲይዝ በማድረግ ቡድናቸውን ይዘው ቀርበዋል፡፡ በዚህ መንገድም ለ23 ደቂቃዎች ያህል ተጫውተዋል፡፡

በ68ኛው ደቂቃ ላይ ግን ፖፓዲች የባንክን ወደ 4-1-4-1 መቀየር በመመልከት ይመስላል ጥላሁን ወልዴን በማስወጣት ሃብታሙ ጥላሁንን ከመስኡድ ጎን እንዲጫወት በማድረግ ለመስኡድ ድጋፍ በመስጠትና በሜዳው ስፋት ለተከላካይ ክፍሉ ሽፋን እንዲሰጥ በማድረግ ለ4-2-3-1 የቀረበ የአጨዋወት ስልትን ተግብረዋል፡፡

የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ሲያገኙ የሚኖራቸው ፍጥነት እና ኳስን ከተጋጣሚ እግር ስር ለመቀማት ያላቸው ተነሳሽነት የቡና ተጫዋቾች ሊጠቀስላቸው የሚገባ ጠንካራ ጎናቸው ነው፡፡ በ62ኛው ደቂቃ ላይ መስኡድ ከቅጣት ምት ጥሩ የጎል ሙከራ አድርጎ አግዳሚ የመለሰበት እና በ91ኛው ደቂቃ ላይ ከመስኡድ የተላከች የማዕዘን ምት በተስፋዬ ኃይሶ በግንባር ተገጭታ በኢማኑኤል ፌቮ የተያዘችው ኳስ ተጠቃሽ የጎል ሙከራዎች ነበሩ፡፡

ምስል 4

buna 1-0 bank image 4

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *