የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ2008 የውድድር ዘመን ረቡእ እና ሀሙስ በተካሄዱ ጨዋታዎች ተከፍቷል፡፡ የመክፈቻ ጨዋታዎችን ተመርኩዞ የተሰናዳውን እውነታ እንድታነቡ ጋብዘናል፡፡
– የመጀመርያውን የማስጠንቀቅያ ካርድ አርቢትር ኃይለየሱስ ባዘዘው የመዘዙ ሲሆን ተስፋዬ መላኩ የተመዘዘበት ተጫዋች ነው፡፡ የመጀመርያ ግብ በኤሌክትሪኩ ፒተር ኑዋድኬ አማኝነት ሲቆጠር የመጀመርያው የፍፁም ቅጣት ምት በድቻው ኃይለየሱስ ብርሃኑ ተመትቶ ግብ ሆኗል፡፡
– ከመጀመርያው ሳምንት ሰባት ጨዋታዎች ስድስቱ በመሸናነፍ ተጠናቀዋል፡፡ ብቸኛው አቻ ውጤት የተመዘገበው በሲዳማ ደርቢ ሀዋሳ ከሲዳማ ቡና 1-1 የተለያዩበት ነው፡፡
– በመክፈቻው ጨዋታዎች 11 ግቦች (በኣማካይ 1,6 ግብ በጨዋታ) ሲቆጠሩ በሁሉም ጨዋታዎች ግቦች ተቆጥረዋል፡፡ አምና በመክፈቻው 13 ግቦች ሲቆጠሩ 2 ጨዋታዎች ካለ ግብ የተጠናቀቁ ነበሩ፡፡
– ቅዱስ ጊዮርጊስ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ በመክፈቻ (1ኛ ሳምንት) ጨዋታ ተሸንፏል፡፡ አዳማ ከነማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በመክፈቻ ጨዋታዎች 3 ጊዜ ተጫውተው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ1992 አአ ላይ 2-1 አሸንፏል፡፡ በ2007 አዳማ ላይ 0-0 ሲለያዩ ዘንድሮ አዳማ 2-0 አሸንፏል፡፡
– ቡና ባንክን በመክፈቻ ጨዋታ ለ3ኛ ጊዜ ገጥሟል፡፡ ትላንት ቡና አሸንፎ ፣ በ1992 አቻ ተለያይተው ፣ በ2007 ባንክ 2-0 አሸንፏል፡፡
– አዳማ ከነማ ቅዱስ ጊዮርጊስን ሲያሸንፍ ከ6 ጨዋታዎች በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ነው፡፡ አዳማ ከነማ ለመጨረሻ ጊዜ ቅዱስ ጊዮርጊስን ያሸነፈው በ2003 የውድድር ዘመን ነው፡፡
– ቅዱስ ጊዮርጊስ በሜዳው አዳማ ከነማ ላይ 100% የማሸነፍ ሪኮርድ ቢኖረውም ወደ አዳማ የሚያደርገው ጉዞ ከፈታኝ ጉዞዎች መካከል ዋነኛው ነው፡፡ የትላንቱን ጨምሮ ከ16 ጉዞዎች ድል ያስመዘገበው በ4 አጋጣሚዎች ብቻ ነው፡፡ 6 አቻ እና 6 ሽንፈት አስመዝግቧል፡፡ አዳማ 17 ሲያስቆጥር ጊዮርጊስ 12 አስቆጥሯል፡፡
– ኤሌክትሪክ በመከላከያ ላይ የያዘውን የበላይነት አስጠብቋል፡፡ መከላከያ በ1997 ወደ ሊጉ ካደገ ወዲህ ከኤሌክትሪክ ጋር ባደረጋቸው 21 ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው በ2 አጋጣሚዎች ብቻ ነው፡፡ ኤሌክትሪክ ረቡዕ መከላከያ ላይ ያስመዘገበው ድል ለ10ኛ ጊዜ የተመዘገበ ነው፡፡
– ዳሽን ቢራ በ2006 ወደ ሊጉ ካደገ ወዲህ ባደረጋቸው 3 የመክፈቻ ጨዋታዎች ግብ አላስተናገደም፡፡ በሁለት አጋጣሚዎች 1-0 ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ካለግብ ተለያይቷል፡፡
– ዘንድሮ ወደ ሊጉ የተመለሰው ድሬዳዋ ከነማ የመክፈቻ ጨዋታ አሸንፎ አያውቅም፡፡ የትላንቱ ሽንፈት 3ኛ ሲሆን 2 ጊዜ አቻ ተለያይቷል፡፡
– ቅዱስ ጊዮርጊስ 11 ተከታታይ ጨዋታዎች በኋላ የመጀርያ ሽንፈት አስተናግዷል፡፡ ከአዳማው ሽንፈት በፊት ለመጨረሻ ጊዜ የተሸነፉት በ2007 የውድድር ዘመን 15ኛ ሳምንት በሀዋሳ ከነማ 2-0 ነው፡፡
– አዳማ ከነማ በሜዳው አስደናቂ ሪኮርድ ይዟል፡፡ አምና ከብሄራዊ ሊግ ከመጣ ወዲህ በሜዳው ባደረጋቸው 14 ጨዋታዎች የተሸነፈው 1 ጊዜ ብቻ ነው፡፡
የመክፈቻ ጨዋታዎች ውጤት
ኤሌክትሪክ 1-0 መከላከያ
ደደቢት 2-1 ወላይታ ድቻ
አዳማ ከነማ 2-0 ቅዱስ ጊዮርጊስ
ሀዋሳ ከነማ 1-1 ሲዳማ ቡና
አርባምንጭ ከነማ 1-0 ሀዲያ ሆሳዕና
ዳሽን ቢራ 1-0 ድሬዳዋ ከነማ
ኢትዮጵያ ቡና 1-0 ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ