መከላከያ 1-0 ኢትዮጵያ ቡና – የጨዋታ ቅኝት

ከዚህ ጨዋታ ቀድሞ የተካሄደው የደደቢት እና የንግድ ባንክ ጨዋታ 0-0 በመጠናቀቁና ይህኛውም የቡና እና የመከላከያ ጨዋታ እስከ 87ኛው ደቂቃ ድረስ ጐል አለማስተናገድ የእለቱን የአዲስ አበባ የስታዲዮም ውሎ ጐሎች የማይቆጠሩበት አስመስሎት ነበር፡፡ ሆኖም ግን በጨዋታው የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የመከላከያው የመስመር አማካይ ሳሙኤል ታዬ ያስቆጠራት ጐል ውጤቱን 0-0 ሆኖ እንዳይጠናቀቅ ታደገው፡፡

በጨዋታው ኢትዮዽያ ቡና ሐሙስ ንግድ ባንክን ከገጠመው ቡድን የቀየረው አንድ ተጫዋች (በመስኡድ ጋቶች ተተክቷል፡፡) ብቻ ቢሆንም የፌርሜሽን ቅያሪ ግን አድርጔል፡፡ ለኤልያስ ማሞ የበለጠ ወደፊት የመንቀሳቀስ ነፃነትን የሰጠ በሚመስል የአማካይ ተከላይነት (Holding Midfielder) ሚና ከሌላኛው የቡድኑ የተከላካይ አማካይ ጋቶች ፓኖሞ ጐን በማሰለፍ 4-2-3-1ን ተጠቅሟል፡፡

የአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌው መከላከያ ደግሞ ቀድሞም ሲጠቀምበት የነበረውን 4-4-2ን (በ4-1-3-2 አቀራረብ) የተጫዋቶች የሜዳ ላይ አደራደር ይዞ ቀርቧል፡፡

(ምስል 1 )

 

የመከላከያዎች የጐንዮሽ ጥበት

የመከላኪያ ሁለቱም የመስመር አማካዮች (ሳሙኤል ታዬ እና ፍሬው ሰለሞን) በሜዳው ቁመት መስመሩን ታከው ወደፊት እና ወደ ኃላ የሚመላለሱ እና ተለምዷዊውን የመስመር አማካዮችን አጨዋወት ባህሪ የተላበሱ ተጫዎቾች አይደሉም፡፡ ይልቁንም ከተሰለፉበት መስመር ኳስን ይዘውም ይሁን ያለኳስ ወደ ውስጥኛው (መሃለኛው) የሜዳ ክፍል መግባትን የሚያዘወትሩ ሆነው ታይተዋል፡፡ ይህ የተጨዋቾቹ እንቅስቃሴ ቡድኑ ጨዋታን ወደ ጐን ለጥጦ የተጋጣሚን የተከላካይ መስመር ተጫዋቾች ወደ ጐን ዘርዘር እንዲሉ በማድረግ (በቡና ተከላካዮች መሃል የሚኖረውን መቀራረብ ወደ መስመሮች ከቦ ክፍተትን መፍጠር) እና ለሁለቱ አጥቂዎች መሃመድ ናስር እና ሞንይሉ ወንድሙ ከመስመር የሚላኩ ተሻጋሪ ኳሶችን እና የአግድሞሽ ቅብብሎችን እንዳያደርጉ ምክንያት ሆኗቸዋል፡፡

ይህ የአጨዋወት መንገድ በጨዋታው የማብቃት ሒደት ላይ መሃለኛው የሜዳ ክፍል የሚኖርባቸውን የተጫዋቾች ቁጥር ብልጫ የሚቀንስላቸው እና የበለጠ ቀጥተኛነትን የሚሰጣቸውን ቢሆንም በመከላከል የአጨዋወት ሂደት ግን ሁለቱን የመስመር ተከላካዮች በቀጥታ ያለሽፋን ወይም ከላላ ተጋላጭ ሲያደርጋቸው ነበር፡፡

በእርግጥ ተጋጣሚያቸው ኢትዮዽያ ቡና ይህን የመከላከያ ክፍል መስመር ለመጠቀም እና በአደገኛ የማጥቃት አጨዋወት ሽመልስ ተገኝ እና ነጂብ ሳኒን ሲፈትን አልታየም፡፡ አልፎ አልፎ የቡናው የቀኝ መስመር አማካይ አብዱልከሪም መሃመድ ወደፊት እየገፋ ለአማካዮች እና አጥቂዎቹ የመቀባበያ አማራጮችን እና መጠነኛ የማጥቃት ማዕዘናትን ከመፍጠሩ ሌላ ይህ ነው የሚባል ተጠቃሽ የማጥቃት እንቅስቃሴ አልተደረገበትም፡፡ መከላከያዎች በነዲብ ሳኒ እና በሽመልስ አማካይነት በመጠኑ ወደፊት እየሄዱ (Overlap እያደረጉ) ለቡድናቸው WIDTH የመስጠት ተግባርን ሲከውኑ ነበር፡፡ በዚህ ሒደት የሚፈጠረውን የChannels ስፋትም (በመሃል ተከላዮች እና የመስመር ተከላካዮች መካከል ያለ ክፍተት) በቡና አጥቂዎች እና አማካዮች ሲፈተሸ አልነበረም፡፡ በሽመልስ እና ነጂስ ቡድናቸው ሲያጠቃ ሁለቱም (Overlap) ያደርጋሉ፡፡ ይህ በሁለቱም መስመሮች በተመሳሳይ ግዜ የሚደረጉ የፊት ለፊት ሩጫዎች (Symmetrical overlapping movement) የሚኖረውን አሉታዊ ጫና ከማጥቃት ወደ መከላከል (Attack-defense Transition) የሚደረግ ሽግግር ላይ በፍጥነት ሲሸፍኑት ታይቷል፡፡

 

mekelakeya 1-0 buna image 2

የአጥቂዎች ተነጥሎ መዋል

የሁለቱም ቡድኖች አጥቂዎች በጨዋታው ላይ የነበራቸው ተሳትፎ አመርቂ አልነበረም፡፡ በተለይ የመከላከያ ሁለቱ አጥቂዎች መሃመድ እና ሞንይሉ ከአማካዮቹ (ሳሙኤል ፣ ሚካኤል እና ፍሬው) ርቀው እና ተነጥለው (Isolated ሆነዉ) አምሽተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ምንይሉ ኳሶችን ከአማካዮች ለመቀበል ወደ ኃላ እና መስመር እየተጠጋ ስለነበር ከመከላከል ወደ ማጥቃት በሚደረገው ሽግግር ላይ በላይኛው የሜዳ ክፍል የሚገኝበት አጋጣሚዎች አናሳ ነበሩ፡፡

አጥቂዎች የሚፈጠሩ እድሎችን በሙሉ ለመጠቀም የሚችሉበት አጋጣሚዎች አንዲፈጠሩ እና የተጋጣሚ ተከላካዮችን የመከላከል አደረጃጀት ለማበላሸት በላይኛው የሜዳ ክፍል በትክክለኛው ሰዓት በብዛት መገኘት ይኖርባቸዋል፡፡ በተለይ የማጥቃት ሽግግሮች ሲካሄዱ፡፡

በጨዋታው የመከላከያ አማካዮች በተለይ ለሁለተኛው አጋማሽ ጥንቃቄን የተመረኮዘ እና ተከላካይ ክፍሉን ይበልጥ የሚያግዝ ወደኃላ ያፈገፈገ ሚና መውሰዳቸው በአጥቂዎቹ እና በአማካዮቹ መሃል የነበረውን ርቀት በማስፋት መሃመድ እና ምንይሉ ይበልጥ እንዲነጠሉ ሆኗል፡፡

የቡናው አጥቂም ተመሳሳይ የመነጠል ሁኔታ ታይቶበታል፡፡ ጥላሁን በብዛት በመከላከል phase ወደ ኃላ ስለሚሳብ እና በሽግግር (Defense-Attack) በቶሎ 1/3ኛ የማጥቃት ወረዳ ላይ ስለማይደርስ በቡና የግራ መስመር የተደረጉ የማጥቃት ውጤቶች እጅግ አናሳ ነበሩ፡፡

ዮሴፍ ዳሙዬም ይበልጥ ለአጥቂው ያቡን ዊሊያም የተጠጋ አቋቋም ላይ ይገኝ ስለነበር ከ Linking-up play (አማካይ እና አጥቂውን የማገናኘት ስራ) ሚናው በላቀ ኳስን የመጠበቅ እና የመቀበል ተሳትፎው ነበረው፡፡ በእርግጥ የዬሴፍ positioning የመከላከያው በኃይሉ ግርማን እጅግ ወደ ኃላ የሳበው ቢሆንም ያን ክፍተት መከላከያዎች በአማዮቻቸው ወደ ኃላ ያፈገፈገ እንቅስቃሴ ሊደፍኑት ችለዋል፡፡ በዚህ የመከላከያ የተደራጀ የሚመስል የመከላከል አቀራረብ የቡና የማጥቃት ሙከራዎች ባብዛኛው የተጋጣሚ ሳጥን ውስጥ ከመድረሳቸው በፊት ሲከሽፍ እና ሲመክኑ ነበር፡፡

የቡና የመሃል ተከላካዮች ወንድፍራው ጌታሁን እና ተስፋዬ ሃይሉ ከተጋጣሚ አጥቂዎች ላይ ኳስን የሚቀሙበት መንገድ ፣ ፍጥነታቸው እና የጨዋታን እንቅስቃሴ የመረዳት ብስለታቸው የተሻለ የነበረ ቢሆንም በመጨረሻ ደቂቃዎች መከላከያዎች ጐሉን ሲያስቆጥሩ የስፋት ፣ ያለመቀናጀት እና ትኩረት ማጣት ችግር በቶሎ መገራት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡

መከላከያዎች በ66ኛው ደቆቃ ቀይረው ያስገቡት ባዬ በመጠኑ የቡና ተከላካዮች ላይ ጫና ለማሳደር ሞክሯል፡፡ ባዬ ከጠንካራ ጐኖቹ አንዱ በሆነው የጐንዮሽ እንቅስቃሴው የተጋጣሚ ተከላካዮች ላይ የሚያሳድረው የመከላከል አደረጃጀት ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም እቅስቃሴው ታክቲካዊ (Tactically Disciplined) ጠቀሜታን ማስገኘት የሚችሉ እንዲሆኑ ማድረግ ቢችል ደግሞ የበለጠ አዎንታዊ ጐኑ ሊጐላ ይችላል፡፡

mekelakeya 1-0 buna image 3

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *