የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ትላንት እና ዛሬ በተደረጉ ጨዋታዎች ቀጥሎ ውሏል፡፡ አዳማ ከነማ እና ዳሽን ቢራ 2ኛ ድላቸውን ሲያስመዘግቡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከድንቅ የጨዋታ እንቅስቃሴ ጋር ሲዳማ ቡናን በሰፊ ግቦች ረቷል፡፡
የእሁድ ጨዋታዎች
ትላንት በአዲስ አበባ ስታድየም ደደቢት ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባደረጉት ጨዋታ 0-0 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይተዋል፡፡ ጨዋታው ለተመልካች የማይስብ እና ቀዝቃዛ የነበረ ሲሆን በግብ ሙከራዎችም አልታጀበም ነበር፡፡ ደደቢት 4 ነጥብ ይዞ 3ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ንግድ ባንክ በ2 ጨዋታ ግብ ማስቆጠር ተስኖታል፡፡
አዳማ ከነማ በሜዳው አይበገሬነቱን በድጋሚ አሳይቷል፡፡ ትላንት በ9፡00 ኤሌክትሪክን አስተናግዶ 2-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል፡፡ አንጋፋው አጥቂ ታፈሰ ተስፋዬ ሁለቱንም የአዳማ ከነማ ግቦች ከመረብ አሳርፏል፡፡ የአዳማ ግቦች በተለይም የመጀመርያው በኤሌክትሪክ ተከላካዮች ስህተት የተገኙ ነበሩ፡፡ በጨዋታው በመጀመርያው አጋማሽ ወንድሜነህ ዘሪሁንን ቀይሮ የገባው ቢንያም አየለ በሁለተኛው አጋማሽ በድጋሚ ተቀይሮ መውጣቱ አስገራሚ ሆኗል፡፡ የኤሌክትሪኩ ግብ ጠባቂ አሰግድ አክሊሉም በጉዳት ተቀይሮ ወጥቷል፡፡
አዳማ ድሉን ተከትሎ ከ2 ጨዋታ 6 ነጥብ እና 4 ንፁህ ግብ ይዞ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አናት ላይ ተቀምጦ ለመጪዎቹ 40 ቀናት ይቀጥላል፡፡
በ11፡30 አዲስ አበባ ስታድየም መከላከያ ኢትዮጵያ ቡናን ገጥሞ 1-0 አሸንፏል፡፡ እንደመጀመርያው የባንክ እና ደደቢት ጨዋታ ሁሉ ይህም ጨዋታ እምብዛም ተመልካች የሚያረካ እንቅስቃሴ ያልታየበት ሲሆን የጦሩን የድል ግብ ከመረብ ያሳረፈው የቀድሞው የቡና የመስመር አማካይ ሳሙኤል ታዬ በ88ኛው ደቂቃ ነው፡፡
የዛሬ ጨዋታዎች
ድሬዳዋ ከ3 የውድድር ዘመን በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ባስተናገደችበት ጨዋታ ድሬዳዋ ከነማ ከ ሀዋሳ ከነማ ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል፡፡ የድሬዳዋን ግብ በእረፍት ሰአት ሱራፌል ዳንኤልን ተክቶ የገባው ፍቃዱ ወርቁ በ50ኛው ደቂቃ ከመረብ ሲያሳርፍ በረከት ይስሃቅ በ87ኛው ደቂቃ ከሁለተኛ ቅጣት ምት (በፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስት የሚሰጥ ቅታት ምት) ግብ አስቆጥሮ ሀዋሳን ነጥብ ተጋርቶ እንዲወጣ አስችሏል፡፡ ከግቧ መቆጠር በኋላ በድሬዳዋ ከነማ እና ዳኞች መካል አለመግባባቶች የነበሩ ሲሆን ጨዋታው ለ10 ደቂዎች ያህል ተረቋርጦ ነበር፡፡
ሀዲያ ሆሳእና በታሪኩ የመጀመርያ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎን በሜዳው አድርጎ በዳሽን ቢራ 1-0 ተሸንፏል፡፡ በሆሳእና ሁለገብ ስታድየም በተደረገው ጨዋታ በርካታ ህዝብ በስቴድየም ተገኝቶ ቡድኑን ቢደግፍም የአሰልጣኝ ግርማ ቡድን ከሽንፈት አልዳነም፡፡ በ57ኛው ሳሙኤል አለባቸው የመታት ኳስ በሆሳእና ተከላካዮች ተጨርፋ ወደ ግብነት ተቀይራ ዳሽንን ለአሸንፊነት አብቅታለች፡፡
በ‹‹ዳንጉዛ ደርቢ›› ወላይታ ድቻ ድል ቀንቶታል፡፡ በቦዲቲ ስታድየም በተደረገው ጨዋታ ወላይታ ድቻ 1-0 በማሸነፍ ከመጀመርያ ሳምንት ሽንፈቱ አገግሟል፡፡ የወላይታ ድቻን የድል ግብ አማካይ አጥቂው በዛብህ መለዮ በ45ኛው ደቂቃ ከመረብ አሳርፏል፡፡
አዲስ አበባ ስታድየም ላይ በተደረገው የዛሬ ብቸኛ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲዳማ ቡናን 5-1 በማሸነፍ ወደ አሸናፊነት ተመልሷል፡፡ ምንያህል ተሾመ በ13ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ግሩም ግብ ለቅዱስ ጊዮርጊስ የእለቱ የመክፈቻ ግብ ስትሆን ብሪያን ኡሞኒ ፣ አዳነ ግርማ እና ራምኬል ሎክ በተከታታይ ግቦች አስቆጥረው ፈረሰኞቹ በ4-0 መምራት ሲችሉ ሲዳማ ቡና በአንዱአለም ንጉሴ የፍፁም ቅጣት ምት ግብ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ቢያደርግም ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር አልቻሉም፡፡ በ90+3ኛው አዳነ ግርማ ተጨማሪ ግብ በፍፁም ቅጣት ምት አክሎ ጨዋታው በቅዱሰ ጊዮርጊስ 5-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
ፕሪሚር ሊጉ ሃገራችን በምታስተናድገው ሴካፋ ምክንያት ለቀጣዮቹ 40 ቀናት የሚቋረጥ ሲሆን የ3ኛ ሳምንት ጨዋታዎችም ታህሳስ 2 ይካሄዳሉ፡፡