ከፍተኛ ሊግ ሀ | ለገጣፎ እና ወልድያ ወደ ድል ሲመለሱ ኤሌክትሪክ የመጀመርያ ሽንፈት አስተናግዷል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ ሰባተኛ ሳምንት ሁሉም ጨዋታዎች እሁድ ተደርገው ወልዲያ፣ ለገጣፎ፣ ደሴ፣ እና ቡራዩ ከተማ አሸንፈዋል።

ዱከም ላይ ቀደም ብሎ በ5:00 የተካሄደው የገላን ከተማ እና ሰበታ ከተማ ጨዋታ 1-1 በሆነ በአቻ ውጤት ተጠናቋል። በ28ኛው ደቂቃ የሊጉን ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት በመምራት ላይ የሚገኘው ኢብራሂም ከድር ሰበታ ከተማን ቀዳሚ ያደረገ ሲሆን ከግቡ መቆጠር በኋላ አጥቂው ደስታውን የገለፀበት መንገድ ትክክል አይደለም በማለት ከገላን ተጫዋቾች ጋር ውዝግብ ውስጥ መግባቱን ተከትሎ በዕለቱ ዳኛ የሁለተኛ ቢጫ (ቀይ) ካርድ ሰለባ ሆኗል። ቀሪውን ክፍለ ጊዜ በጎደሉ ተጫዋቾች የተጫወተው ሰበታ ከተማ ተጨማሪ አንድ ተጫዋች (ታደለ ባይሳ) በሁለተኛው አጋማሽ በቀይ ካርድ ያጡ ሲሆን ገላኖች የአቻነት ጎል አስቆጥረው ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎ የ9:00 ጨዋታዎች እስኪካሄዱ ድረስ ሰበታ ከተማ በጊዜያዊነት በ14 ነጥቦች የሠንጠረዡ አናት ላይ መቀመጥ ችሎ ነበር። 

ለገጣፎ ላይ መሪው ለገጣፎ ለገዳዲ አክሱም ከተማን አስተናግዶ በጌትነት ደጀኔ እና ሱራፌል አየለ ጎሎች 2-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል። በወሎ ኮምቦልቻ የዓመቱ የመጀመርያ ሽንፈት ደርሶበት የነበረው ለገጣፎ ወደ ድል መመለሱን ተከትሎ የምድቡ አንደኝነት አስጠብቆ መጓዝ ችሏል። 

ወልዲያ ላይ በ10:00 ወሎ ኮምቦልቻን ያስተናገደው ወልዲያ ከእረፍት በፊት በተቆጠረች ብቸኛ ጎል 1-0 በማሸነፍ ደረጃውን ማሻሻል ችሏል። 

ባደረጉት ከእረፍት በፊት ወልድያዋች ባገቡት ብቸኛ ግብ ወሎ ኮምበልቻን በማሸነፍ የደረጃ ሰንጠረዣቸውን ማስተካከል ችለዋል ።

ከአሰልጣኙ ኃይለየሱስ ጋር የተለያየው ደሴ ከተማ በሜዳው ፌዴራል ፖሊስን አስተናግዶ 1-0 ሸነፍ ችሏል። የደሴን ብቸኛ የድል ጎል በ88ኛው ደቂቃ ያስቆጠረው አትክልት ንጉሴ ነው። 

ቡራዩ ላይ ቡራዩ ከተማ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ያደረጉት ጨዋታ በቡራዩ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። አብዱልከሪም የብቸኛዋ የድል ጎል ባለቤት ነው። በውጤቱ መሠረት በመጀመርያዎቹ ስድስት ሳምንታት ሽንፈትም ሆነ ጎል ያላስተናገደው ኢትዮ ኤሌክትሪክ የውድድር ዓመቱኝ የመጀመርያ ሽንፈት እና ጎል ለማስተናገድ ተገዷል። 

ኒያላ ሜዳ ላይ አቃቂ ቃሊቲ ከ አውስኮድ ያደረጉት ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል። አውስኮዶች ሙክታር ሀሰን ባስቆጠረው ጎል መሪ መሆን ቢችሉም አቃቂ ቃሊቲዎች ባገኙት ፍፁም ቅጣት ምት በመጠቀም ሳምሶን ተሾመ አስቆጥሮ አቻ መሆን ችለዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *