የአሰልጣኞች አስተያየት | ወልዋሎ 1-0 ባህር ዳር ከተማ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 11ኛ ሳምንት መቐለ ላይ ወልዋሎ ባህር ዳር ከተማን አስተናግዶ 1-0 ካሸነፈ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። 

“ቡድናችን ሜዳ ላይ ጥሩ ነበር፤ ውጤቱም ይገባናል” ፀጋዬ ኪዳነ ማርያም – ወልዋሎ

ስለ ጨዋታው

የዛሬው ጨዋታ እስካሁን ካደረግናቸው ጨዋታዎች የተሻለ እና ጥሩ የኳስ ፍሰት ያሳየንበት እኖዲሁም ብዙ የግብ ዕድሎች የፈጠርንበት ነበር። በነጥብ ደረጃ ተቀራርበን ነው ይህን ጨዋታ ያደረግነው። በዚህ ምክንያት የግድ ጨዋታውን ማሸነፍ አለብን ብለን ነበር እየሰራን የነበረው። በሜዳ የነበረው እንቅስቃሴም የዚህ አንድ ማሳያ ነው።

ቡድናችን ዛሬ በብዙ መለክያዎች የተሟላ ነበር። ጥሩ ተከላክለናል፤ ጥሩ አጥቅተናልም። በመጀመርያው አጋማሽ ብዙ ያለቀላቸው የግብ እድሎች ፈጥረናል። ከዚ በላይም አሸንፈን የምንወጣበት ዕድል ነበረን። በአጠቃላይ ቡድናችን ሜዳ ላይ ጥሩ ነበር፤ ውጤቱም ይገባናል።

የሜዳውን ጨዋታ መቐለ ላይ የማድረግ ተፅዕኖ

ምንም ለውጥ የለውም። ግን ደጋፊዎቻችን እየተንገላቱ ነው። ደርሶ መልስ መመላለስ ለዛውም ከጨዋታ በኋላ አስራ አንድ ሰዓት ወይም አስራ ሁለት ሰዓት ወደ ዓዲግራት ጉዞ መጀመር ከባድ ነው። በአጨዋወታችን ላይ ግን የፈጠረው ተፅዕኖ የለም።

ቡድኑ ብዙ የግብ ዕድሎች ስለማምከኑ

አዎ። በቀላሉ ግብ አናስተናግድም፤ ያገኘነው የግብ ዕድል የመጠቀም ችግርም አለብን። ይህ ችግር የመጣውም  ሁለት አጥቂዎች ብቻ ናቸው። ከአንደኛው ጋርም ከጥቂት ጊዚያት በኃላ በስምምነት እንለያያለን ብየ አስባለው። አንድ የውጭ ተጫዋች ለማምጣትም ስራዎችን ጀምረናል፤ በሁለተኛው ዙር ይደርሳል ብዬ አስባለው። አሁን ካለው አጥቂዎች ችግር አንፃር ባደረግነው እንቅስቃሴ ግን ደስተኛ ነኝ።

በስቴድየም ተገኝቶ ለደገፈን የወልዋሎ ዓድግራት ደጋፊ እና የመቐለ ነዋሪ ማመስገን እፈልጋለው፤ ድጋፋቹ አይለየን እላለው። ከዋንጫ ፉክክር ብዙም አልራቅንም ወደ ላይ ደረጃችን የማናሻሽልበት ምክንያት የለም። አሁንም በርካታ ጨዋታዎች አሉብን። ከቀሩት ጨዋታዎች ሁለት በሜዳችን እና ሁለት ከሜዳችን ውጭ ነው የምንጫወተው። እንደውም ሶስተኛውም በሜዳችን እንደምንጫወት ነው ማስበው ከስሑል ሽረ ጋር ስለሆነ። በቀጣይ ያሉብንን ጨዋታዎች አሸንፈን ቡድናችንን ጥሩ ደረጃ ላይ እናስቀምጣለን።

ስለ ቀጣይ ጨዋታቸው

ቀጣይ ጨዋታችን ከአዳማ ጋር ነው። አዳማ ከተማ በሜዳው ጠንካራ ቡድን ነው። ነገር ግን ፈርተን አንገባም። ትንሽ ሚያሰጋን የሬችሞንድ አዶንጎ ጉዳት ነው። የስድስት ቀን ፋታ ስላለን ወደ ሙሉ ጤናው ከተመለሰ ሌላው ቡድናችን በጥሩ ሁኔታ ነው ያለው። ከዚ ውጭ በቀጣይ ጨዋታ አስራት መገርሳ ስለሚመለስ ጥሩ ለመጫወት ጥረት እናደርጋለን።

“በኳሱ የሁለቱ ክልል ወንድማማችነት እየጠነከረ መሄዱ ለሃገር ሰላም እና አንድነት ጥሩ ነው” ጳውሎስ ጌታቸው

ስለ ጨዋታው

ጨዋታው እንዳያችሁት ነው ብዙም የምለው ነገር የለም። ሁሉም ነገር ተመልክታችሁታል። ከዕረፍት በኋላ ብልጫ ነበረን። ተጋጣሚያችን ግን ሜዳ ላይ በመተኛት ጨዋታው አልቋል። ዕድል እስካለህ ድረስ ማንም መጠቀም ይችላል። ግን ባጠቃላይ ጨዋታው ለኔ ጥሩ ነበር።

በጨዋታው አንዳንድ ስህተቶች ነበሩ። ያ ስህተት በምን እንደሚታረም አላውቅም። ማለት የዳኝነት ስህተት ነበር። እንደተመለከታችሁት የጭማሪው ደቂቃ ላይ አራት ደቂቃ ነው የተጨመረው። ግብ ጠባቂው ብቻ አራት ደቂቃ ተኝቷል። ብዙ ስለ ዳኛ ማውራት አልፈግም፤ ወልዋሎዎች በማሸነፋቸው እንኳስ ደስ አላቸው።

ስለ መቐለ ቆይታቸው

ደጋፊው በ ስነ-ስርዓት ተቀብሎናል። ምንም ያጋጠመን ነገር የለም። ያለው ነገር በአጠቃላይ ጥሩ ነው፤ ለኳሱ እድገት ሲባል ሁሉም በጋራ ለኳሱ እድገት መጣር እና ሌላውን ነገር መተው ነው።

በዳንኤል ኃይሉ አለመኖር ቡድኑ ተጎድቷል?

ምንም የተጎዳው ነገር የለም። በቃ እንደተመለከታችሁት ነው፤ ምክንያቱም አጥቅተን ነው የተጫወትነው። ብዙ ዕድሎች አምክነናል። ይሄ የዳንኤል ሃይሉ አለመኖር ጉዳይ አይደለም። መጀመርያ የተሰጠብንን ፍፁም ቅጣት ምት ካሜራቹ ከያዘው ደጋግማችሁ እዩት፤ በደምብ ተመልከቱት። ያለውን ነገር በፀጋ ነው የተቀበልነው። ምክንያቱም ምንም ጭቅጭቅ አያስፈልግም የዳኛው የግል ዕይታ ነው። ተጫዋቾቼ የሚፈለገውን መስዋዕትነት ከፍለዋል። በዚ አጋጣሚ ላመሰግናቸው እወዳለው።

ስለ ሁለቱ ክልል ክለቦች

በቃ እኔ የማስተላልፈው መልእክት ስለ ኳሱ ነው። በእንደነዚህ አይነት ጨዋታዎች ላይ ዛሬ የመጣው ስምምነት ነገ እንዳይደፈርስ በተለይ በዳኞች አወሳሰን ላይ በጣም በጣም የጠነከረ ውሳኔ ሊወሰን ይገባል። ምክንያቱም ህዙቡን የሚያነሳሳው የዳኛው ጉዳይ ነው። የዳኛ ጉዳይ ላይ በተለይ በሁለቱም ክልል ክለቦች ጨዋታ ላይ   በጣም ሊታሰብበት ይገባል። በኳስ የበለጠው ያሸንፍ፤ እኛ በዚ ነው ምናምነው። በኳሱ የሁለቱም ክልል ወንድማዊነት እየጠነከረ መሄዱ ለሃገር ሰላም እና አንድነት ህብረት ጥሩ ይሆናል ብለን ስለምንገምት ይሄ ቢቀጥል ደስተኛ ነኝ።

ከሜዳ ውጪ ሁለት ተከታታይ ሽንፈት ስለማስተናገዱ

እንግዲህ ባጠቃላይ የሽንፈት ጉዳይ በቡድናችን የተጀመረ አይደለም። ካደረግናቸው ጨዋታዎች አራት አሸንፈን፣ ሶስት ግዜ አቻ ወጥተን፣ ሁለት ግዜ ደሞ ተሸንፈናል። አሁንም በዋንጫ ፉክክር ውስጥ ነው ያለነው። ይህን ነገር እንደምናስቀጥል እርግጠኛ ሆኜ መናገር እፈልጋለው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *