ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና መሪነቱን አጠናክሯል

በአዲስ አበባ ስታድየም በተደረገው የዕለቱ ብቸኛ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ሀዋሳ ከተማን አስተናግዶ በሱለይማን ሎክዋ ግብ 1-0 መርታት ችሏል።

ሁለቱም ቡድኖች በአስረኛው ሳምንት ካደረጓቸው ጨዋታዎች ውስጥ ሁለት ሁለት ለውጦችን አድርገዋል። ኢትዮጵያ ቡና ከሲዳማ ነጥብ ከተጋራበት ጨዋታ ሚኪያስ መኮንንን እና የአምስት ቢጫ ካርድ ቅጣት ያለበት አቡበከር ነስሩን በዳንኤል ደምሴ እና የኋላሸት ፍቃዱ ሲተካ ሀዋሳ ከተማ ደግሞ ከመቐለው ሽንፈት በሁለቱ የመስመር ተመላላሾች ዳንኤል ደርቤ እና ደስታ ዮሃንስ ቦታ ያኦ ኦሊቨርን እና አስጨናቂ ሉቃስን አስጀምሯል።

ጨዋታው በጀመረ ጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ግብ የተቆጠረበት ነበር። በፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን ከረጅም ርቀት ሙከራ በማድረግ የጀመሩት ሀዋሳዎች ባልተለመደ ሁኔታ በአራት የኋላ መስመር ተከላካዮች ነበር የገቡት። ሆኖም ጨዋታው እንደጀመረ የቀኙ የቡድኑ የተከላካይ ክፍል በቂ ሽፋን ያገኘ አይመስልም። በመሆኑም 6ኛው ደቂቃ ላይ ዳንኤል ደምሴ መሀል ላይ ከነጠቀው ኳስ ያቀበለውን የኋላሸት በዚሁ አቅጣጫ ይዞ በመግባት ሲያሻግርለት ሎክዋ ሳይቸገር በግንባሩ ወደ ግብነት ለውጦታል። ከግቡ በኋላ እስከ ሠላሳኛው ደቂቃ አካባቢ ኳስ ይዘው በቡና የሜዳ አጋማሽ ለመቆየት የቻሉት ሀዋሳዎች የመጨረሻ የግብ ዕድል ማግኘት ግን አልሆነላቸውም። የታፈሰ ሰለሞን ተፅዕኖ ወርዶ በታየበት እና የአማካይ ክፍሉ ቅርፅ ለቡና የኋላ መስመር ፈታኝ ባልሆነባቸው በነዚህ ደቂቃዎች እስራኤል እሸቱ እና አዳነ ግርማ ወደ ኋላ ተስበው ቅብብሎችን ለመከውን ይሞክሩ ነበር። ቡድኑ ከተጋጣሚው ተከላካይ መስመር ፊት ክፍተትን ሲያገኝም የማጥቃት ሽግግሩ ፈጣን ስላልነበረ 29ኛው ደቂቃ ላይ አስጨናቂ ሉቃስ ካደረገው ሌላ የረጅም ርቀት ሙከራ ውጪ አደገኛ አጋጣሚ መፍጠር አልቻለም። 

በጊዜ መምራት የቻሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች ከግቡ በኋላ በራሳቸው ሜዳ ላይ ቆይተው የተጋጣሚያቸውን ስህተቶች መጠበቅ መርጠዋል። ኳስ በሚነጥቁባቸው ጊዜያትም ልክ ግቡን ባገኙበት መንገድ በተለይም በአህመድ ረሺድ በኩል ፈጥነው ወደ ሀዋሳ አጋማሽ ለመግባት ይጥሩ ነበር። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ 15 ደቂቃዎች ሲቀሩት ጀምረው ግን ባለሜዳዎቹ አብዛኛውን ጊዜያቸውን ወደ ሀዋሳ ግብ ክልል ቀርበው ነበር ያሳለፉት። ሆኖም ከካሉሻ አልሀሰን እና ሳምሶን ጥላሁን ወደ ፊት ይጣሉ የነበሩት ኳሶች ሁለቱ አጥቂዎች ጋር ሳይደርሱ ከግብ ክልሉ ወጥቶ ኳስ በሚያርቀው ሶሆሆ ሜንሳህ ሲድኑ በተደጋጋሚ ይታይ ነበር። አጋማሹ ሊጠናቀቀቅ አካባቢም ኢትዮጵያ ቡና ከፈጠረው ከዚሁ ጫና በርከት ያሉ የቆሙ ኳሶችን ማግኘት ቢችልም ሁለተኛውን ግብ ለማግኘት የሚረዳ ግልፅ የግብ ዕድል መፍጠር ሳይችል ቡድኖቹ ወደ ዕረፍት አንርተዋል።

ከእረፍት መልስ ጨዋታው በመጀመሪያው አጋማሽ የታየበት መቀዛቀዝን ተላብሶ ነበር የጀመረው። ሆኖም ከሀዋሳ ተከላካዮች ጀርባ የመግባት በርካታ አጋጣሚዎች የነበሯቸው ቡናዎች 47ኛው ደቂቃ ላይ አህመድ ከተከላካዮች ከነጠቀው ኳስ ለየኋላሸት ሰጥቶት አጥቂው ከጨዋታ ውጪ የሆነበት 55ኛው ላይ ደግሞ በድጋሜ የኋላሸት ከሎክዋ ተቀብሎ ወደ ሳጥን በደረሰባቸው ዕድሎች የተጋጣሚያቸውን ክፍተት አሰይተዋል። እንደመጀመሪያው ሁሉ የቡናን የመከላከል አደረጃጀት ለመስበር ጥረታቸውን የቀጠሉት ሀዋሳዎች ተነቃቅቶ በታየው ታፈሰ ላይ ተነስርተው ወደ ፊት በመግፋት ለመጫወት ሞክረዋል። ነገር ግን 62ኛው ደቂቃ ላይ ኄኖክ ድልቢ ከርቀት ካደረገው ሙከራ ውጪ አሁንም ከግብ ጠባቂ ጋር የሚያገናኛቸውን ዕድል ማግኘት ቸግሯቸዋል።  

ቀጣዮቹ ደቂቃዎች ለኢትዮጵያ ቡና በርካታ የግብ ዕድሎችን ይዘው የመጡ ነበሩ። ሳምሶን ጥላሁን ከቅጣት ምት አልሀሰን ካሉሻ ደግሞ በጨዋታ ከረጅም ርቀት ካደረጓቸው ሙከራዎች ውጪ ቡድኑ በተደጋጋሚ ከሀዋሳ የኋላ ክፍል ጀርባ መድረስ ችሏል። ነገር ግን የሶሆሆ ሜንሳህ ንቃት እና የሀዋሳ የጨዋታ ውጪ መረብ ለቡና አጥቂዎች ተጨማሪ ዕድሎች አለማግኘት ምክንያት ሆነዋል። ያም ቢሆን 67ኛው እና 80ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ ሲንቀሳቀስ ከዋለው ዳንኤል ደምሴ የተነሱት ኳሶች የግብ ልዩነቱን ለማስፋት ተቃርበው ነበር። ሆኖም የመጀመሪያውን ካሉሻ ከኋላሸት ተቀብሎ ከሶሆሆ ጋር ተገናኝቶ በማይታመን መልኩ ሲያመክነው ሁለተኛውን ሎክዋ በግንባር ሞክሮ ስቶታል። 

ረጃጅም ኳሶችን ወደ ፊት በመጣል የአቻነት ግብ ፍለጋቸውን ያላቋረጡት ሀዋሳዎችም 87ኛው ደቂቃ ላይ እጅግ ከባድ ሙከራ አድርገዋል። አዲስዓለም ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ ተቀይሮ የገባው ገብረመስቀል በግንባሩ ሲሞክር ኳስ እና መረብ ሳይገናኙ የቀሩት በግብ ጠባቂው ኢስማ ዋቴንጋ አስገራሚ ብቃት ነበር። በስድስቱ ጭማሪ ደቅቃዎችም እስራኤል ከሳጥን ውስጥ ያደረገው የመቀስ ምት ሙከራ ለጥቂት ነበር ኢላማውን ሳይጠብቅ የቀረው። ጨዋታው በዚህ መልኩ ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያ ቡና በ22 ነጥቦች መሪነቱን ሲቀጥል ሀዋሳ ከተማ ወደ ሦስተኝነት ወርዷል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *