ሳሙኤል ዮሐንስ ስለ እግርኳስ ህይወቱ እና ስላሳለፈው አስቸጋሪ የልጅነት ጊዜ ይናገራል

” እናቴ በህይወት የለችም። እሷ ስታርፍ አባቴ ስላልነበረ ሐረር በሚገኘው የህፃናት ማሳደጊያ ማደግ ጀመርኩ። ማሳደጊያው ሲፈርስ ወደ ባህርዳር የህፃናት ማሳደጊያ በማምራት እግርኳስን መጫወት ጀመርኩ “

በባህርዳር ከተማ በሚገኝ ፕሮጀክት ነበር የእግርኳስ ህይወቱን የጀመረው፣ ከ2007 ጀምሮ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እስከፈረሰበት ጊዜ ደረስ  ከተስፋ ቡድኑ እስከ ዋናው ቡድን መጫወት ችሏል። አምና ወደ ከፍተኛ ሊግ ተሳታፊ ለነበረው አማራ ውሃ ስራ ለአንድ ዓመት ቆይታ አድርጎ ዘንድሮ ደግሞ ለፕሪምየር ሊጉ ክለብ ድሬዳዋ ከተማ ፊርማውን በማኖር እስካሁን በሁሉም የቡድኑ ጨዋታዎች ላይ ተሳትፎ አድርጓል። ከድሬዳዋ ጋር በግሉ ጥሩ የውድድር ጊዜ እያሳለፈ የሚገኘው እና በክለቡ ደጋፊዎች ልብ መግባት የቻለው የግራ መስመር ተከላካዩ ሳሙኤል ዮሐንስ ስላለፈበት አስቸጋሪ የልጅነት ህይወቱ እና የእግርኳስ ህይወቱ የእስካሁን ጉዞ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ያደረገውን ቆይታ እንዲህ አሰናድተነዋል።

ትውልድ እና እድገትህ የት ነው?

የተወለድኩት ሐረር ከተማ ነው። እናቴ በህይወት የለችም። እሷ ስታርፍ አባቴ ስላልነበረ ሐረር በሚገኝ <ሆተ ምስራቅ> በሚባል የህፃናት ማሳደጊያ ማደግ ጀመርኩ። ማሳደጊያው ፈርሶ ሰባት ልጆች ባህር ዳር ወደሚገኘው ሚካኤል የህፃናት ማሳደጊያ ሲላኩ አንዱ ሆኜ አብሬ ተጓዝኩ። ይህ ነው አስተዳደጌ።

ወላጅ አባትህን ለማግኘት አልሞከርክም?  እህት ወንድሞችስ አሉህ ? 

አባቴን ወታደር በመሆኑ ማግኘት አልቻልኩም። በህይወት እንዳለ እሰማለሁ፤ ግን አላገኘሁትም። አንድ ቀን አገኘው ይሆናል። ቤተሰቦች እንዳሉኝ ቢነገረኝም አንዳቸውንም ግን እስካሁን ማግኘት አልቻልኩም። ሆኖም ለማግኘት ጥረት እያደረኩ ነው። 

ወደ እግርኳስ ተጫዋችነት የመጣህበት መንገድ እንዴት ነው ?

ባህርዳር የህፃናት ማሳደጊያ እያለው ጣና ባህርዳር በተባለ ፕሮጀክት ታቅፌ እሰራ ነበር። የፕሮጀክቱ አሰልጣኝ የአሁኑ ኢኮስኮ ዋና አሰልጣኝ የሆነው ደግያረጋል ይግዛው ነው። እሱ ጋር ስድስት ዓመት ከሰራው በኋላ ነበር 2007 ላይ ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተስፋ ቡድን ያመራሁት። ከአንድ ዓመት በኋላ ወደ ዋናው ቡድን አድጌ ሁለት ዓመት በመጫወት ንግድ ባንክ ሲፈርስ ወደ ባህርዳር አምርቼ ለአማራ ውሃ ስራ ለአንድ ዓመት በመጫወት ቆይቼ ዘንድሮ ድሬዳዋ ከተማን መቀላቀል ችያለው።

በህፃናት ማሳደጊያ ውስጥ ማደግህ እግርኳስ ተጫዋች ለመሆንህ የሰጠህ ጠቀሜታ አለ? 

ህፃናት ማሳደጊያ ውስጥ የነበረኝ ቆይታ ለዛሬ እግርኳስ ህይወቴ በእጅጉ ረድቶኛል። ማሳደጊያ ጣቢያ ውስጥ የእግርኳስ መጫወቻ ሜዳዎች አሉ። እዛ ነው እየተጫወትኩ ያደግኩት። ከዛ ባሻገር የህይወትን ፈተና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኜ ማለፌ በእዕምሮው ረገድም ጠንካራ እንድሆን ረድቶኛል።

በንግድ ባንክ በተወሰኑ ጨዋታዎች ላይ የመሰለፍ እድል አግኝተህ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ እያደረክ ባለህበት ሰዓት ነበር ቡድኑ የፈረሰው። ክለቡ መፍረሱ ምን አይነት ስሜት ፈጠረብህ? የት ሄጄ እጫወታለው ብለህስ አልሰጋህም?

በጊዜው አብዛኛዎቻችን ወጣቶች ነበርን። ነገን ተስፋ በማድረግ ጥሩ ነገር እየሰራን ቡድኑ ከነበረበት የውጤት መንሸራተት ለመመለስ ጥረት እያደረግን ነበር። ቡድኑ ግን ከመውረድ ሊተርፍ አልቻለም። በወቅቱ ሁላችንም የቡድኑ አባላት ወደ ሌላ ክለብ መሄድን አላሰብንም ነበር። ይሄን ትልቅ ክለብ ወደ ቀደመው ክብሩ ዳግም ለመመለስ እያሰብን ባለንበት ሰዓት ያላሰብነው ነገር ተከሰተ፤ ቡድኑ መፍረሱን ሰማን። ይህ ለእኔ በጣም ከባድ ነበር። በጊዜው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ትልቅ ቡድን ስለነበር ይፈርሳል ብዬ አላሰብኩም። በእኛ ዘመን መፍረሱ ደግሞ ስሜቱ በጣም ከባድ ነው። ተስፋ ትቆርጣለህ፤ ጭንቀት ውስጥም ትገባለህ። እኔንጃ በጊዜው የነበረው ስሜት እንዲህ ነው ብለህ ለመግለፅ ትቸገራለህ። ከባድ ወቅት ነበር።

ከንግድ ባንክ በመቀጠል ያመራኸው ወደ አማራ ውሃ ስራ ነበር፤ እዛ የነበረህን ቆይታ እንዴት ትገልጸዋለህ ?

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲፈርስ ወደ ባህርዳር ሄድኩኝ። እዛም በከፍተኛ ሊግ ተሳታፊ ለሆነው አውስኮድ ለአንድ ዓመት ያህል ተጫወትኩ ። የቡድኑ አጠቃላይ ውጤት ጥሩ ባይሆንም በግሌ ራሴን ወደተሻለ ደረጃ ለማሳደግ ጠንክሬ ሰርቻለው፤ አቅሜን ለማሳደግም ከፍተኛ ሊግ መጫወቴ እጅግ በጣም ጠቅሞኛል። ብዙ ነገር ተምሬበታለው። ድሬዳዋ ከተማ ለዝግጅት ባህር ዳር ሲመጣ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ የሙከራ እድል ሰጥቶኝ ዕድሉን ተጠቅሜ አቅሜን በማሳየቴ ነው ድሬዳዋን ዘንድሮ መቀላቀል የቻልኩት።

ወደ ድሬደዋ ያመራኸው በሙከራ ነው ?

አዎ በሙከራ ነው። አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ በግል አያውቀኝም፤ በዝግጅት ወቅት ለወጣቶች የሙከራ እድል እየሰጠ ስለነበር እኔም እድል አግኝቼ ከሁለት እና ሦስት ሙከራ በኋላ አሰልጣኝ ዮሐንስን አሳምኜ ነው በክለቡ መያዝ የቻልኩት። በእዚህ አጋጣሚ አሰልጣኝ ዮሐንስን ማመስገን እፈልጋለው። በወጣቶች በማመን እና ዕድል በመስጠት፣ አቅማቸውን እንዲያሳድጉ በመምከር እና በማሰልጠን ትልቅ ችሎታ አለው። እኔ አቅሜን አውጥቼ እንድጠቀም ትልቅ አስተዋፆኦ አድርጎልኛል፤ በጣም ነው የማመሰግነው። 

እስካሁን ባለው የድሬዳዋ ቆይታህ ጥሩ የሚባል የውድድር ጊዜ እያሳለፍክ ነው። በተመልካች እና ደጋፊዎች ዘንድም ከፍተኛ ተወዳጅነት እያተረፍክ ነው። የእስካሁን ቆይታህ ምን ይመስላል ?

እውነት ለመናገር እግርኳስን በጥሩ ሁኔታ የመጫወት ስኬቴን “ሀ” ብዬ የጀመርኩት እዚህ (ድሬዳዋ) እንደሆነ ነው የማስበው። እዚህ በመምጣቴ በጣም ደስተኛ እና ውጤታማ እየሆንኩ ነው። ከቀን ወደ ቀን፣ ከጨዋታ ጨዋታ በራሴ ላይ ለውጦች እና መሻሻሎችን እያየሁ ነው። የእኔን አጨዋወት ተመልክተው ጥሩ አስተያየት እየሰጡኝ ነው። ይህ ነገር አሁን ላይ ጥሩ ነገር እንድሰራ ሞራል ሆኖኛል። ወደፊትም ጥሩ ነገር ይገጥመኛል ብዬ አስባለው።

በግልህ ጥሩ እንቅስቃሴ አድርግ እንጂ ድሬዳዋ አሁን ያለበት ጊዜያዊ የውጤት ጉዞ ጥሩ የሚባል አይደለም። ከአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌም ጋር ተለያይቷል። ቡድኑ በአሰልጣኝ ለውጥ ሽግግር ላይ መሆኑ በቀጣይ ጉዞው ላይ ተፅዕኖ ይኖረዋል ብለህ ታስባለህ ?

መጀመርያ አካባቢ ላይ ያሰባሰበን አሰልጣኝ ዮሐንስ ስለነበረ እና ከሱ ስንሰራ በመቆየታችን በመልቀቁ ትንሽ አለመረጋጋት ነበር። ሆኖም ምክትል አሰልጣኝ ስምዖን ዓባይ ቡድኑን ከያዘው በኋላ ጥሩ መነሳሳት አለ። ምክንያቱም አሰልጣኝ ይመጣል ይሄዳል፤ ይህ የእግርኳስ ባህሪ ነው። አሁን ላይ ቡድናችን በዚህ ሁለት ጨዋታ የመንሸራተት ነገር እየታየ ነው። በሒደት ራሳችንን እያስተካከልን እና እየተሻሻልን እንመጣለን ብዬ አስባለሁ።

በአሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ከ20 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለመጀመርያ ጊዜ ጥሪ ተደርጎልህ ከሶማልያ ጋር የደርሶ መልስ ጨዋታ መጫወት ችለሀል። የብሔራዊ ቡድን ጥሪህን እንዴት አገኘኸው ? 

እውነት ለመናገር ያላሰብኩት ጥሪ ነው። ምክንያቱም ከከፍተኛ ሊግ ቡድን ነው የመጣሁት። ይህን ዓመት ቢያንስ ባለሁበት ክለብ ጥሩ የውድድር ዓመት ማሳለፍን እንጂ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጥሪን አልጠበኩም። ምን አልባት ለጥሪው የረዳኝ በመጀመርያው የሊጉ መርሐ ግብር አዲስ አበባ ላይ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ባደረግነው ጨዋታ ጥሩ መንቀሳቀስ መቻሌ ነው። ከጥሪው በኋላ በራስ መተማመኔ በጣም ጨምሯል፤ በራሴ ላይ ከቀን ወደ ቀን ለውጥ እያየሁ ነው። ከዚህ በኋላም በብሔራዊ ቡድን የመጫወት ከፍተኛ ፍላጎት አለኝ። ብሔራዊ ቡድን በእኔ ቦታ ክፍተት አለ፤ በተፈጥሮ ግራኝ የሆነ ብዙ ተጫዋች እየተገኘ አይደለም። ይህንን ችግር ለመቅረፍ ጠንክሬ እሰራለው።

በየጨዋታዎቹ የተለዩ ቴክኒካል እንቅስቃሴዎችን ታደርጋለህ። ኳሱን ቀለል አድርገህ ነው የምትጫወተው። ይህ ደግሞ ተመልካቹን እያዝናናው ይገኛል። ይህ ክህሎት ከምን የመጣ ነው? በኢትዮጵያ ያልተለመደውን ነፃነት እና በራስ መተማመን እንዴት አገኘኸው ?  

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፈረሰ በኋላ አውስኮድ በነበረኝ ቆይታ በፕሪምየር ሊጉ እና በከፍተኛ ሊግ ያለው የመጫወት ስሜት ይለያያል። በከፍተኛ ሊግ ጫና ባለመኖሩ በግልህ ማድረግ የምትፈልገውን ለማድረግ ጊዜ ስለምታገኝ ደጋግመህ ለመስራት ትሞክራለህ። በዚህ ነው በራስ መተማመኔ እና ይህን ክህሎቴን እንዳሳይ ምክንያት የሆነኝ። በዚህ አጋጣሚ እንደ ተጫዋች ለነገ እግርኳስ ህይወትህ ብዙ ልምድ ማግኘት ካሰብክ በከፍተኛ ሊግ ተጫውቶ ማለፉ ጠቀሜታ አለው። ምክንያቱም ነፃነት አለ፤ ከዛ ባለፈ የሚከፈልህ ደሞዝ አነስተኛ በመሆኑ ለማደግ ስትል ጠንክረህ ትሰራለህ።

ሌላው በእግርኳሳችን ላይ ብዙም የማይታየው የመስመር ተከላካዮች በማጥቃት ላይ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ነው። ይህን አጨዋወት በተደጋጋሚ እንድታሳይ የረዳህስ ምንድነው ? 

እውነት ለመናገር በፊት እንደዚህ አልጫወትም ነበር። መጀመርያ እግርኳስን መጫወት ስጀምር የአማካይ ስፍራ ተጫዋች ነበርኩ። ግራኝ እንደመሆኔ መጠን አሰልጣኞች ናቸው ወደ መስመር ወጥቼ እንድጫወት ያደረጉኝ። ኳስን ይዤ እንድጫወት እና ወደ ፊት ሄጄ እንዳጠቃ እየነገሩኝ ነው እንዲህ መጫወት የቻልኩት። ድሬዳዋ ከመጣሁም በኋላ አሰልጣኞቼ በእኔ በኩል እንድናጠቃ እና በቀኝ በኩል ደግሞ እንድንከላከል መደረጉ ወደ ፊት ሄጄ እንድጫወት በጣም ጠቅሞኛል። አሁንም ግን ብዙ ማሻሻል የሚገቡኝ ነገሮች ስላሉ በቀጣይ እያስተካከልኩ እሄዳለው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *