ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ሲዳማ ቡና ከ መከላከያ

ሲዳማ ቡና መከላከያን በሚያስተናግድበት የ12ኛ ሳምንት ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል። 

በ11ኛው ሳምንት ደቡብ ፖሊስን በመርታት ወደ ድል የተመለሱት ሲዳማ ቡናዎች ከዋንጫ ፉክክሩ ሸርተት ያሉ ቢሆንም ወቅታዊ አቋሙ ጥሩ ያልሆነው መከላከያን ያስተናግዳሉ። ከሁለት የ 5-1 ሽንፈቶች በኋላ ድል ለማጣጣም ተቃርቦ የነበረበትን የሽረ ጨዋታ አሳልፎ የሰጠው መከላከያ ሦስት ነጥቦችን ካሳካ አንድ ወር ሆኖታል። ቡድኑ ቀስ በቀስ እየተንሸራተተም አሀን 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ያላቸው ሲዳማዎች ከመሪው ጋር ያላቸው የነጥብ ልዩነት አምስት የደረሰ ሲሆን በሜዳቸው ከሚያደርጉት የነገው ጨዋታ ውጤትን ማሳካት እስከ ሁለተኝነት ከፍ ያደርጋቸዋል። ሦስት ጨዋታዎች እጁ ላይ የሚገኙት መከላከያም ወደ ሰንጠረዡ አጋማሽ መጠጋት የሚችልበት ዕድል ይኖረዋል። ጨዋታው እስካሁን በሜዳው እጅ ያልሰጠን እና ከሜዳው ውጪ ሽንፈት ያላገኘውን ቡድን የሚያገናኝ በመሆኑ ማን ሪከርዱን ያስቀጥላል የሚለውንም ጥያቄ የሚመልስ ይሆናል። 

ሲዳማ ቡና ግርማ በቀለን ከአምስት ቢጫ ካርድ ቅጣት ዳግም በቀለን ደግሞ ከጉዳት መልስ ሲያገኝ ግብ ጠባቂው መሣይ አያኖ ቢያገግምም ለነገው ጨዋታ አይደርስም። ዳዊት እስጢፋኖስ እና ግብ ጠባቂው አቤል ማሞን በጉዳት ምክንያት የሚያጣው መከላከያ በስሑል ሽረው ጨዋታ ጉዳት ያስተናገደው ሽመልስ ተገኝንም አገልግሎትም አያገኝም። በሌላ በኩል ተከላካዩ አበበ ጥላሁን ከጉዳቱ የተመለሰ ሲሆን ቅጣት ላይ የሚገኘው ተመስገን ገብረኪዳን ግን ከስብስቡ ውጪ ነው።

ከሲዳማ ቡና የሜዳው ላይ አቋም አንፃር ሲታይ የመከላከያ የወቅቱ የመከላከል ችግር በጨዋታው ላይ ትልቅ ተፅዕኖ የሚኖረው ይመስላል። ከፍተኛ ጫና በመፍጠር በተለይም ከመስመር በሚነሱ አጥቂዎቹ በኩል ደጋግሞ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመግባት የሚጥረው ሲዳማ ቡና አማካይ ክፍል ላይ ብልጫ ሊወሰድበት ቢችልም የጦሩን ግራ እና ቀኝ የመከላከል ክፍል የመፈተን አቅም ይኖረዋል። በጉዳት እና ቅጣት ተደጋጋሚ ለውጦች የሚደረጉበት የመከላከያ የኋላ ክፍል ትልቁ ፈተናም የአዲስ ግደይ እና ሀብታሙ ገዛኸኝን ፍጥነት መቋቋም ላይ ነው። የማጥቃት ባህሪ ካላቸው አማካዮቹ ቅብብሎች እንዲሁም በተለይ ከቴዎድሮስ ታፈሰ ረጃጅም ኳሶች ለአጥቂዎቹ የግብ ዕድል መፍጠር ደግሞ የመከላከያ የማጥቃት አማራጭ እንደሚሆን ይጠበቃል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን 18 የእርስ በርስ ግንኙነት አድርገዋል። ሰባቱ ጨዋታዎች በአቻ ውጣት ሲጠናቀቁ ሲዳማ ስድስት መከላከያ ደግሞ አምስት ጊዜ ድል ቀንቷቸዋል። ተመጣጣኝ ቁጥር ባለው ግንኙነታቸው ሲዳማ 15 መከላከያ ደግሞ 14 ግቦችን አስቆጥረዋል።

– የከተማ ተቃናቃኞቹ ሀዋሳ ከተማ እና ደቡብ ፖሊስ የተገናኘባቸውን ጨምሮ ሀዋሳ ላይ ሰባት ጨዋታዎችን ያደረገው ሲዳማ ቡና አራቱን በድል አጠናቆ በሦስቱ ነጥብ ተጋርቷል። እስካሁን በሜዳው ሽንፈት አልገጠመውም።

– ካሉት ዘጠኝ ነጥቦች አምስቱን ከሜዳው ውጪ ያገኘው መከላከያ ከሦስት ጨዋታዎች ነበር ውጤቶቹን የሰበሰበው። በድል ያጠናቀቀው ጨዋታም ሀዋሳ ላይ ከደቡብ ፖሊስ ጋር የተገናኘበት ነበር።

ዳኛ

– በአምስተኛ እና ዘጠነኛ ሳምንታት ላይ ሁለት ጨዋታዎችን መርቶ የነበረው ዮናስ ካሳሁን ይንን ጨዋታ ይዳኛል። አርቢትሩ በሁለቱ ጨዋታዎች ሰባት የቢጫ ካርዶችን መዟል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሲዳማ ቡና (4-3-3)

ፍቅሩ ወዴሳ

ዮናታን ፍሰሀ – ሚሊዮን ሰለሞን – ሰንደይ ሙቱኩ – ፈቱዲን ጀማል

ዳዊት ተፈራ  – አበባየሁ ዮሀንስ – ግርማ በቀለ

ሀብታሙ ገዛኸኝ – መሀመድ ናስር –  አዲስ ግደይ

መከላከያ (4-4-2 ዳይመንድ)

ይድነቃቸው ኪዳኔ 

ምንተስኖት ከበደ –  አዲሱ ተስፋዬ – አበበ ጥላሁን – ታፈሰ ሰረካ

ቴዎድሮስ ታፈሰ

ሳሙኤል ታዬ – ዳዊት ማሞ

ፍሬው ሰለሞን

ፍፁም ገብረማርያም – ምንይሉ ወንድሙ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *