ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | መቐለ 70 እንደርታ ከ ኢትዮጵያ ቡና 

ከነገ ሦስት ጨዋታዎች መካከል ተጠባቂ የሆነውን የመቐለ 70 እንደርታ እና ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ የተመለከቱ ጉዳዮችን እንደሚከተለው አዘጋጅተንላችኋል።

በተጋጣሚያቸው ጅማ አባ ጅፋር የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ጨዋታ ምክንያት በ 11ኛው ሳምንት ጨዋታ ያላደረጉት መቐለዎች ነገ 09፡00 ከሊጉ መሪ ኢትዮጵያ ቡና ጋር ይገናኛሉ። ሲዳማ ቡና እና ሀዋሳ ከተማን በተከታታይ ማሸነፍ የቻሉት መቐለዎች ከአራተኛው ሳምንት በኋላ ከታየባሸው መቀዛቀዝ የተነቃቁ ይመስላሉ። በዚህ ሰዓት ላይ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር መገናኘታቸው ደግሞ የጨዋታውን ዋጋ ከፍ የያደርገዋል። እንደ መቐለ ሁሉ የመጨራሻ ጨዋታዎቹን ከሲዳማ እና ሀዋሳ ጋር ያደረገው ኢትዬጵያ ቡና አሁን በሊጉ አናት እንደተቀመጠ ይገኛል። ከባህር ዳሩ ሽንፈት በኋላ አራት ድሎችን ማስመዝገብ መቻሉም እንሰተጋጣሚው ሁሉ መልካም አቋም ላይ ስለመገኘቱ ምስክር ነው። በነጉው ጨዋታም ኢትዬጵያ ቡና መሪነቱን ይበልጥ ለማስፋት መቐለ ደግሞ እስከ አምስተኛነት ከፍ ለማለት እንደሚፋለሙ ይጠበቃል።

በሲዳማው ጨዋታ ጉዳት ያገጠመው የመቐለው አማካይ ሳሙኤል ሳሊሶ እና ተከላካዩ አቼምፖንግ አሞስ ልምምድ ቢጀምሩም ሙሉ ለሙሉ ብቁ ባለመሆናቸው ለነገው ጨዋታ እንደማይደርሱ ሲታወቅ በእጁ ላይ ጉዳት የደረሰው አሸናፊ ሃፍቱም ሌላ በጨዋታው ማይሰለፈው የባለሜዳዎቹ ተጫዋች ነው። አማኑኤል ዮሃንስን ከጉዳት መልስ እንደሚያገኝ የሚጠበቀው ኢትዮጵያ ቡና ቶማስ ስምረቱን እና ልምምድ የጀመረው አስራት ቱንጆን ይዞ አልተጓዘም ፤ አቡበከር ናስር ደግሞ ከቅጣት መልስ ክለቡን እንደሚያገለግል ይጠበቃል።

መቐለ 70 እንደርታ በጨዋታው የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን በማግኘት ላይ ተመስርቶ እንዲሁም ድንገተኛ ክፍተቶች ሲገኙ በቶሎ ወደ ግብ ለመድረስ በመሞከር በማጥቃት ላይ ተመስርቶ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይጠበቃል። በተለይም ከአማኑኤል ገብረሚካኤል በሚነሳ የመስመር ጥቃት የመጨረሻ የግብ ዕድል የሚፈጥሩት መቐለዎች ከኢትዮጵያ ቡና ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ብሩት ፍልሚያ ይጠብቃቸዋል። ግብ ካስቆጠረ በኋላ ጥንቃቄ የተሞላበት አቀራረብን ምርጫው ያደረገው የአሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስ ቡድን የመስመር ተመላላሾቹን ጨምሮ በመከላከል ወቅት ባለአምስት የኋላ መስመር ሲይዝ በቀላሉ ክፍተት አይሰጥም። በመሆኑም የማጥቃት ባህሪ ያላቸው የባለሜዳዎቹ አማካዮች ይህን ፈተና ለማለፍ የሚጠቀሙት መንገድ ከወዲሁ ተጠባቂ ነው። ከዚህ ውጪ የአልሀሰን ክሉሻ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ቀርቦ መጫወት እና የዳንኤል ደምሴ የተሳኩ ረጃጅም ኳሶች ለኢትዮጵያ ቡና ነገም ከተከላካይ መስመር ጀርባ የግብ ዕድሎችን የሚያስገኙበት ዕድል የሰፋ ሲሆን ደካማ ሆኖ የታየው የቡድኑ አጨራረስ ችግር ግን ዕንቅፋት እንዳይሆንበት ያሰጋዋል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– መቐለ ሊጉን በተቀላቀለበት የአምናው የውድድር ዓመት ሁለቱ ቡድኖች መቐለ ላይ የተገናኙበት ጨዋታ ያለግብ ሲጠናቀቅ በ30ኛው ሳምንት ኢትዮጽያ ቡና 3-1 ድል ማድረግ ችሏል።

– መቐለ 70 እንደርታ በትግራይ ስታድየም ካደረጋቸው አራት ጨዋታዎች ሦስቱን አሸንፎ በአንዱ ነጥብ ተጋርቷል። 

– እስካሁን አራት ጊዜ ከአዲስ አበባ የወጣው ኢትዮጵያ ቡና አንድ ጊዜ በድል ሲመለስ ሁለቴ የአቻ አንዴ ደግሞ የሽንፈት ውጤቶች ገጥመውታል።

– ሀለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ ሁኔታ የመጨረሻ የሊግ ሽንፈት ያገኛቸው በስድስተኛው ሳምንት ነበር። መቐለ ወደ አዳማ ተጉዞ የ3-1 ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ወደ ባህር ዳር ሄዶ የ1-0 ሽንፈት ገጥሟቸው ነበር። 

ዳኛ

– ጨዋታው ለብርሀኑ መኩሪያ የዓመቱ ሦስተኛ ጨዋታው ይሆናል። ከዚህ ቀደም በአራተኛው እና ሰባተኛው ሳምንታት በዳኘባቸው ሁለት ጨዋታዎችም ሦስት የማስጠንቀቂያ ካርዶችን ብቻ አሳይቷል።

ግምታዊ አሰላለፍ

መቐለ 70 እንደርታ (4-2-3-1)

ፍሊፔ ኦቮኖ 

ስዩም ተስፋዬ – አሌክስ ተሰማ – አሚኑ ነስሩ – አንተነህ ገብረክርስቶስ

ጋብርኤል አህመድ – ሚካኤል ደስታ 

አማኑኤል ገብረሚካኤል – ሐይደር ሸረፋ – ዮናስ ገረመው

ያሬድ ከበደ

ኢትዮጵያ ቡና (3-4-2-1)

ዋቴንጋ ኢስማ

ተመስገን ካስትሮ – ክሪዝስቶም ንታምቢ – ወንድይፍራው ጌታሁን

          
አህመድ ረሺድ –  ዳንኤል ደምሴ – ሳምሶን ጥላሁን – እያሱ ታምሩ

                 
ካሉሻ አልሀሰን  – አቡበከር ናስር

 ሱለይማን ሎክዋ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *