ስሑል ሽረ የነገውን ጨዋታ በቴክኒክ ዳይሬክተሩ እየተመራ ያከናውናል

በዚህ ዓመት ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ፕሪምየር ሊግ ያደገውና በውጤት ማጣት ውስጥ የሚገኘው ስሑል ሽረ የቡድኑ ደጋፊዎች ሲያቀርቡት የነበረው ጥያቄን መሠረት በማድረግ አሰልጣኙ፣ ረዳት አሰልጣኙ እና የቡድን መሪው በነገው ጨዋታ ላይ እንደማይኖሩ ሲገለፅ የነገው ጨዋታንም በቴክኒክ ዳይሬክተሩ እየተመራ እንደሚያደርግ ለማወቅ ተችሏል።

በሊጉ ባደረጋቸው አስር ጨዋታዎች ሰባት የአቻ ውጤቶች አስመዝግቦ ምንም ድል ሳያደርግ በ7 ነጥቦች 13ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ሽረ በተለይ በሜዳው በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ከደጋፊዎች ተቃውሞ ሲያስተናግድ ቆይቷል። በዚሁ የደጋፊዎች ተደጋጋሚ ጥያቄ መነሻነትም ክለቡ ዋና አሰልጣኙ ዳንኤል ፀሐዬ፣ ምክትሉ በረከት ገብመድኅን እና የቡድን መሪው ኤፍሬም ሓድሽን በጊዜያዊነት በሌሎች መተካቱ ታውቋል። በ12ኛው ሳምንት ነገ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር በሜዳው የሚያደርገውን ጨዋታም በቴክኒክ ዳይሬክተሩ ገብረ ኪሮስ አማረ እየተመራ ይገባል ተብሏል። 

የአሰልጣኞቹ እና የቡድን መሪው ቀጣይ እጣፈንታ ያልታወቀ ሲሆን ከነገው ጨዋታ በኋላ አልያም በቀጣዮቹ ቀናት የክለቡ ቦርድ ስብሰባ አድርጎ የቆይታቸው ወይም የመልቀቃቸው ነገር እርግጥ እንደሚሆን ይጠበቃል።

ነገ ቡድኑን በጊዜያዊነት እንደሚመሩ የሚጠበቁት ገብረ ኪሮስ በ1990 በሐጎስ ደስታ እየተመራ የመጀመርያው የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ያነሳው የመብራት ኃይል ቡድን ተጫዋች የነበሩ ሲሆን በትራንስ ኢትዮጵያ፣ ጉና ንግድ፣ ወንጂ ስኳር እና  ድሬዳዋ ምድር ባቡር እንዲሁም በ1989 ለኢትዮጵያ ወጣት ብሄራዊ ቡድን ተጫውተው አሳልፈዋል። በ1997 ከተጫዋችነት ከተገለሉ በኋላም በመቐለ 70 እንደርታ፣ ራያ ዓዘቦ፣ ስሑል ሽረ እና ትግራይ ውሃ ስራ በአሰልጣኝነት ሰርተዋልል። በ2008 ስሑል ሽረን ወደ ከፍተኛ ሊግ እንዲያድግ ያገዙት ገብረ ኪሮስ ከሁለት ዓመት ቆይታ በኋላ ወደ አሰልጣኝነት የሚመለሱም ይሆናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *