ቴድሮስ አለማው ያቢዮ የአጥቂ መስመር ተሰላፊ ነው፡፡ በፍጥነቱ፣ ግብ ማስቆጠር አቅሙ እና በፊት መስመር የተለያዩ ቦታዎች በመጫወት የሚታወቀው ቴድሮስ የመጀመሪያ ዲግሪ የህግ ተማሪም ነው፡፡ ቴድሮስ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ስለእግርኳስ ህይወቱ በተመለከተ ቆይታ አድርጓል፡፡
ቴድሮስ አለማው ያቢዮ የተወለደው ከኢትዮጵያዊያን ቤተሰቦች ታህሳስ 5 1985 ሱዳን ውስጥ ነው፡፡ ቤተሰቦቹ ከጎንደር ሲሆኑ በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረውን የእርስበርስ ጦርነት ሸሽተው ካገራቸው የተሰደዱ ነበሩ፡፡ ቴድሮስ ስለተወለደባት ሱዳን ብዙም ትዝታ የለውም፡፡
“የተወለድኩት ሱዳን ነው ቤተሰቦቼ ከጎንደር ናቸው፡፡ በሱዳን ስለነበረኝ ቆይታ ምንም የማስታውሰው ነገር የለም፡፡ ለሶስት ዓመታት ከቤተሰቤ ጋር በሱዳን ቆይታ አድርጊያለው፡፡ በ1988 ቤተሰቦቼ ጋር ወደ አድሌድ አውስትራሊያ ተሰደን አመራን፡፡ ትልቅ ቤተሰብ አለኝ በአጠቃላይ 8 ወንድሞች እና እህቶች አሉኝ፡፡”
ገና በህፃንነቱ ወደ አውስትራሊያ ያመራው የ23 ዓመቱ ቴድሮስ በአድሌድ አውስትራሊያ የመናፈሻ ፓርኮች እግርኳስን መጫወት እንደጀመረ ይናገራል፡፡
“እግርኳስን መጫወት የጀመርኩት በአድሌድ የመናፈሻ ፓርኮች ውስጥ ነበር፡፡ አድሌድ ትንሽ ከተማ ነበረች እኔ እና ቤተሰቦቼ ለከተማዋ አዲስ መሆናችን ባህሉን እና ቋንቋ ለመልመድ አስቸግሮን ነበር፡፡ ከወንድሞቼ ጋር በመሆን ወደ ፓርክ በመሄድ ከሌሎች በአውስትራሊያ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አባላት ጋር ኳስ እንጫወት ነበር፡፡ መጀመሪያ አከባቢ ከአውስትራሊያዊያን ጋር በቋንቋ ስለምናግባባ ብቸኛው የመግባቢያ መሳሪያ እግርኳስ ነበር፡፡”

በመናፈሻ ፓርኮች ኳስን ማንከባለል የጀመረው ቴድሮስ የመጀመሪያ ደረጀ ትምህርቱን እየተከታተለ ለሚኖርበት ከተማ ክለብ ተመለመለ፡፡
“የአንደኛ ደረጃ ተማሪ በነበርኩበት ወቅት አደሌድ ኦሎሚፒክ የተባለ ክለብ ውስጥ የመጫወት ዕድል አግኝቼ ወደዛው አመራው፡፡ በክለቡ ውስጥ በየደረጃው የሚሰጡ ትምህርቶችን እና ልምምዶችን እየሰራው ቆየው፡፡ በክለቡ በነበረኝ ተሳካ ቆይታ በሌሎች የአድሌድ ክለቦች ዕይታ ውስጥ ገባው፡፡ አደሌድ ኦሎሚፒክን ከለቀቅኩ በኃላ ክሮይደን ኪንግስ ለተባለ ክለብ ከ14 ዓመት በታች ቡድን ለመጫወት ችያለው፡፡”
ለቴድሮስ በአድሌድ ኦሎምፒክ እና ክሮይደን ኪንግስ የነበረው ቆይታ በሚገባ ጠቅሞታል፡፡
“በሁለቱ ክለቦች በነበረኝ የተሳካ ቆይታ ምክንያት ለክልሌ ታዳጊ ቡድን ተጠራው፡፡ የደቡብ ቪክቶሪያ ቡድንን ወክዮ መጫወት ቻልኩ፡፡ ሻምፒዮን በሆንንበት ውድድርም በፍፃሜ ጨዋታ ግብ አስቆጠርኩ፡፡ በመቀጠል ቪክቶሪያ ኢንቲትዩት ኦፍ ስፓርት በ1998 በተመቻቸልኝ ዕድል ልገባ የቻልኩት፡፡ በስፓርት መዐከሉ የተሻለ ስልጠና አግኝቼለው፡፡ ለሁለት ዓመት በነበረኝ የማዕከሉ ቆይታዬ ከቪክቶሪያ ግዛት ጋር በግዛቶች ከ15 ዓመት በታች የእግርኳስ ውድድር ላይ እስከፍፃሜ ደርሻለው፡፡”
በቪክቶሪያ ኢንቲትዩት ኦፍ ስፓርት የሁለት ዓመት ቆይታው ለቴድሮስ የተሻሉ ዕድሎች ከፋች ነበር፡፡
“በኢንስቲትዩቱ በነበረኝ የተሳካ ቆይታ ለአውስትራሊያ ከ16 ዓመት ከዛም ለ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን ተመርጥኩ፡፡ በ2000 በነበረኝ ጥሩ አቋም ለአውስትራሊያ ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ብድን ተጠርቼ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ተጫውቻለው፡፡ በነገራችን ላይ ለ17 ዓመት ብሄራዊ ብድን ስጫወት አብሮኝ የተጫወተው ሌላው ኢትዮጵያዊ የመስመር አማካይ ከማል ኢብራሂም ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ሰፈሬ ውስጥ በወዳጅነት ጨዋታ ላይ የተመለከቱኝ የኤ ሊግ ቡድን የሆነው ሜልቦርን ቪክትሪ መልማዮች ወደ ክለቡ ወጣቶች ቡድን አመጡኝ፡፡ መልማዮቹ በአውስትራሊያ ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ብድን ስጫወት ተመልክተውኝ ስለነበረ ወደ ሜልቦርን ቪክትሪ ወጣት ብድን ሊያመጡኝ ቻሉ፡፡”
በ2001 ቴድሮስ ለኤ ሊጉ ክለብ ሜልቦርን ቪክትሪ ለመጫወት ቻለ ውሉን አኖረ፡፡
“ለሜልቦርን ቪክትሪ ዋና ቡድን ለመጫወት ግዜም አልፈጀብኝም፡፡ ለቅድመ ውድድር ዝግጅት ወደ ቻይና ከዋናው ቡድን ጋር ሄድኩኝ፡፡ ከቅድመ ውድድር ዝግጅት በኃላ በድጋሚ ወደ ወጣት ቡድኑ ተመለስኩኝ፡፡ ነገርግን በ2002 መጨረሻ ያጋጠመኝ አስከፊ ጉዳት ከክለቡ እንድለይ አስገደደኝ፡፡ በግዜው 18 ዓመቴ ነበር፡፡ ክለቡ ከኔ ጋር የነበረውን ውል አቋረጠ፡፡ እስካሁን በክለቡ የተገፋው መስለኛል፡፡ ክለቡን አለመጥቀሜ ያበሳጨኛል፡፡ ያጋጠመኝ ጉዳት በጣም አስከፊ በመሆኑ ለ2 ዓመታት ከምወደው እግርኳስ ተለየው፡፡ አብዛኛውን ግዜዬን ታናናሽ ወንድሞቼን በመንከባከብ እንዲሁም ከጉዳት ለማገገም በመሞከር አሳለፍኩ፡፡”

ለ2 ዓመታት ቆይታ በኃላ የአጥቂ መስመር ተሰላፊው ቴድሮስ እግርኳስን መጫወት ዳግም ጀመረ፡፡
“ከ2 ዓመት በኃላ እግርኳስን መጫወት ጀመርኩ፡፡ አዲስ ክለብ ማግኘት በጣም ፈተና ነበር፡፡ በስተመጨረሻም በቪክቶሪያ ናሽናል ሊግ የሚወዳደር ሴንት አልባን ሴንት የእግርኳስ ክለብ እንድጫወትላቸው ጥሪ አቀረቡልኝ፡፡ እኔም ጥያቄውን ተቀብዬ በክለቡ እየተጫወትኩ እገኛለው፡፡ እስካሁን ያጋጠመኝ የከፋ ጉዳት የለም፡፡ በአዲሱ ክለቤ መጫወት ከጀመርኩ ግዜ አንስቶ አንድ ግዜ ብቻ ነው የተጎዳሁት፡፡”
የጀርመን ስደተኞች በመሰረቱት ሴንት አልባን ሴንት የእግርኳስ ክለብ (በ1960ዎቹ መጨረሻ ክሮሺያዊያን ስደተኞች ክለቡን ማስተዳደር ጀምረዋል) እየተጫወተ የሚገኘው ቴድሮስ ታናሽ ወንድሙ ሰለሞን በዚው ክለቡ ወጣት ብድን በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡ ቴድሮስ በአውሮፓ ከሚገኙ ክለቦች ጋር በፈጠረው ግንኙነት ወደ አውሮፓ በማቅናት የሙከራ ግዜ እንዲያሳልፍ ተጋብዟል፡፡
“ከአንዳንድ ሰዎች ጋር በመነጋገር በጀርመን 2ኛ እና 3ኛ ዲቪዚዮን እና ሆላንድ 2ኛ ዲቪዚዮን ክለቦች የሙከራ ዕድል አግኝቼያለው፡፡ በሙከራ ግዜ ውስጥ የተሻለ ነገር አሳይቼ አውሮፓ ውስጥ መጫወት እፈልጋለው፡፡ ህልሜን እንደማሳከ ተስፋ አደርጋለው፡፡ በአውሮፓ የሚኖረኝ የሙከራ ግዜ ካልተሳካ በቀጣይነት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጫወት ከፍተኛ ፍላጎት አለኝ፡፡ የኢትዮጵያ እግርኳስን በቅርበት አላውቀውም፡፡ የተለየ የእግርኳስ ባህል እና የጨዋታ ስልት እንዳለ እረዳለው፡፡ ይህንን የእግርኳስ ባህል ማወቅ እና መማር በእጅጉ እፈልጋለው፡፡ አማርኛ መናገር አለመቻሌ በይበልጥ በሊጉ የመጫወት ፍላጎቴን ይጨምራል ምክንያቱም የአማርኛ ቋንቋ መማር እፈልጋለው፡፡”

ለሙከራ በሙኒክ ከተማ የሚገኘው ቴድሮስ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጫወት ፍላጎት እንዳለው እንዳልሸሸገ ሁላ ለኢትዮጵያ ቡሄራዊ ብድን የመጫወት ዕድል ካገኘ እንደሚጫወት ይናገራል፡፡
“ምንም ጥያቄ የለውም ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ብድን ያለምንም ማቅማማት እጫወታለው፡፡ ቤተሰቦቼ ኢትዮጵያን እንድወድ አርገው ነው ያሳደጉኝ፡፡ ማንነቴን እና ደሜ ከየት እንደሆነ በደንብ አውቃለሁ፡፡ ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡”