‹‹ ጋና ላይ ግብ አስቆጥራለሁ ብዬ አስባለሁ ›› ሎዛ አበራ

የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን ለአለም ዋንጫ ጉዞው ወሳኝ የ90 ደቂቃ መንገድ ቀርቶታል፡፡ በመጪው እሁድ ኩማሲ ላይ ከጋና ከ20 አመት በታች ሴቶች ብ/ቡድን ጋር የመልስ ጨዋታውን የሚያደርገው ብሄራዊ ቡድናችን ዛሬ ቀትር ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም የመጨረሻ ልምምዱን አድርጓል፡፡ በኩማሲ ከፍተኛ ሙቀት የሚጠብቃቸው በመሆኑ የሰሞኑ ልምምዶቻቸው ፀሃዩ በሚያይልባቸው ሰአቶች ሆኗል፡፡

በአዲስ አበባ ስታድየም ከ10 ቀን በፊት በተደረገው የመጀመርያ ጨዋታ 2-2 አቻ የተለያዩት ወጣቶቹ ሉሲዎች በመልሱ ጨዋታ የጠበበ እድል ይዘው ቢጓዙም በድል ለመመለስ የቻሉትን እንደሚያደርጉ አምበሏ ሎዛ አበራ እና አሰልጣኝ አስራት አባተ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡

‹‹ ባለፉት ቀናት ጥሩ ልምምድ ሰርተናል፡፡ አሸንፈን ለመመለስ እየተዘጋጀን ነው፡፡ ›› ያለችው ሎዛ አበራ ብሄራዊ ቡድኑ በሷ ትከሻ እዚህ ደርሷል የሚሉ አስተያየቶችን እንደማትቀበል ትናገራለች፡፡

‹‹ … እንደዛ ብዬ አላምንም ምክንያቱም እግርኳስ የቡድን ስራ ነው፡፡ ሁሉም ተቀባብሎ ነው ኳሱ አጥቂዎች ጋር የሚደርሰው፡፡ አጥቂ ግብ ማግባት ስለሚጠበቅበት ግብ ያስቆጥራል እንጂ ሁሉም ለውጤቱ ይለፋል፡፡ ›› ብላለች፡፡

በ5 ጨዋታዎች 6 ግብ በማስቆጠር በማጣርያው ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን እየመራች የምትገኘው ሎዛ ከኩማሲ ግብ አስቆጥራ እንደምትመለስ ያላትን እምነት ገልጻለች፡፡ ‹‹ … አዎ፡፡ ጋና ላይ ግብ አስቆጥራለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ ››

IMG_7926

‹‹ ከሜዳችን ውጪ ጠንካራ መሆናችንን አሳይተናል ›› አሰልጣኝ አስራት አባተ

አሰልጣኝ አስራት አባተ የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ሴቶች ብሄራዊ ቡድንን በመምራት ወደ አለም ዋንጫ ለማሳለፍ ከፊታቸው ከባድ ፈተና ቢጋረጥባቸውም ጋናን ለማሸነፍ የሚያስችል ዝግጅት እንዳደረጉ ተናገረዋል፡፡

‹‹ ከጋናው ጨዋታ መልስ የተሻለ ጥሩ ዝግጅት አድርገናል ብለን እናስባለን፡፡ ከሌላው ጊዜ የተሻለ የዝግጅት ጊዜም አግኝተናል፡፡ በ13 ቀን 3 ጨዋታ ማድረጋችን ጫና ፈጥሮብን ነበር፡፡ ድካምም ነበረብን፡፡ አሁን ግን የተጫዋቾቼ የድካም ሁኔታ መስተካከል ችሏል፡፡

‹‹ ተጫዋቾቹ የኢንተርናሽናል ጨዋታ ልምድ የሌላቸው ናቸው፡፡ ቡድኑም የ4 ወር ብቻ እድሜ ነው ያለው፡፡ ያም ቢሆን ልጆቹ የማሸነፍ ፍላጎታቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ከእለት እለት ጥሩ እየተማሩ ያሉ ልጆች ናቸው፡፡ የኛ ቡድን ከሜዳው ውጪ ግብ በማስቆጠርና በማሸነፍ የተሻለ ሪኮርድ ያለው ቡድን ነው፡፡ ይህም ከሜዳ ውጪ ማሸነፍ እንደሚችሉ ያሳያል፡፡ እስካሁን በ5 ጨዋታ ሽንፈት አላስተናገድንም፡፡ ባለችን ትንሽ ልምድ ጋናን ፈትነን እናልፋለን የሚል ግምት አለን፡፡ ያ ደግሞ ለሃገራችን የሴቶች እግርኳስ እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ ስላለው በተሻለ ትኩረት ተንቀሳቅሰንና ኳስ ተቆጣጥረን እናሸንፋለን፡፡ ›› ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ነገ ጠዋት 2፡00 ላይ በረራውን የሚጀመርር ሲሆን በኩማሲ ከጋና ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ ካሸነፈ አልያም ከ2 ግብ በላይ በሆነ አቻ ውጤት ከተለያየ በቀጣዩ የፈረንጆች አመት በፓፓ ኒው ጊኒ አስተናጋጅነት ለሚደረገው የአለም ከ20 አመት በታች ሴቶች ዋንጫ ከሚያልፉት 2 ቡድኖች አንዱ ይሆናል፡፡

መልካም እድል ለወጣት ቡድናችን፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *