ጌታነህ እና ዋሊድ ለኮንጎው ጨዋታ ሲጠሩ ሳላዲን በጉዳት አይደርስም

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ወደ አለም ዋንጫ ማጣርያ የምድብ ማጣርያ ዙር ለመግባት ከሪፑብሊክ ኦፍ ኮንጎ (ብራዛቪል) ጋር ለሚያደርገው የደርሶ መልስ ጨዋታ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ 23 ተጫዋቾችን ከሃገር ውስጥ 3 ተጫዋቾችን ደግሞ ከውጭ ሃገራት ክለቦች ጥሪ አድርገዋል፡፡

ከሳኦቶሜ ጋር በተደረገው ጨዋታ በመቀነሳቸው የሚድያ መነጋገርያ ሆነው የሰነበቱት ጌታነህ እና ሳላዲን እንዲሁም በገንዘብ እጥረት ወደ ሳኦቶሜ መጓዝ ያልቻለው ዋሊድ አታ ወደ ብሄራዊ ቡድኑ የሚመልሳቸው ጥሪ የደረሳቸው ሲሆን ሳላዲን ከጉዳቱ በሚገባ ባለማገገሙ ከኮንጎው ጨዋታ ውጪ ሆኗል፡፡

የፌዴሬሽኑ የህዝብ ግንኙነት አቶ ወንድምኩን አላዩ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደተናገሩት ዮሃንስ ለሶስቱ ተጫዋቾች ጥሪ ይደርሳቸዋል፡፡

‹‹ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ በውጭ ሃገራት የሚጫወቱ 4 ተጫዋቾችን የጠሩ ሲሆን ሳላዲን ባለፉት 2 ሳምንታት ከልምምድ በመራቁ እና ከጉዳቱ ለማገገም እረፍት እንደሚያስፈልገው በመናገሩ ከኮንጎው ጨዋታ ውጪ ሆኗል፡፡ ሽመልስ ፣ ጌታነህ እና ዋሊድ ከነገ ጀምሮ ይፋዊ ጥሪ የሚደረግላቸው ሲሆን እስከ እሁድ ድረስ አዲስ አበባ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለወሳኙ የደርሶ መልስ ጨዋታ እንዲረዳው የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ ያቀደ ሲሆን ሁኔታዎች ከተመቻቹ ከብሄራዊ ቡድኖች ካልሆነ ደግሞ ከሃገር ውስጥ ክለቦች ጋር በመጫወት የተጫዋቾችን ወቅታዊ አቋም ለማወቅና ለኮንጎው ጨዋታ የሚሆኑ ተጫዋቾችን ለመምረጥ ታስቧል፡፡

ኢትዮጵያ የአለም ዋንጫ 2ኛ የቅድመ ማጣርያ ጨዋታዋን ከሪፑብሊክ ኦፍ ኮንጎ ጋር በመጨው ኖቬምበር 14 (ህዳር 4) በአዲስ አበባ ስታድየም ስታደርግ የመልስ ጨዋታዋን ኖቬምበር 17 (ህዳር 7) በብራዛቪል ታደርጋለች፡፡ ይህን ማጣርያ ካለፈችም 20 ቡድኖች በሚካፈሉበት የምድብ ድልድል ውስጥ ትገባለች፡፡ በ5 ምድቦች ተከፍሎ የሚደረገውን የምድብ ማጣርያ የሚያልፉ 5 ሃገራትም በ2018 ሩስያ ለምታስተናግደው የ21ኛው የአለም ዋንጫ ያልፋሉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *