በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የ2015 የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ሃገራት ውድድር የሚሳተፉ ሃገራት 10 መድረሳቸውን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡
ውድድሩን አስመልክቶ ከ2 ሳምንታት በፊት በኢሊሊ ሆቴል በተሰጠው መግለጫ ላይ በሴካፋ ውድድር እንደሚካፈሉ የተረጋገጡት ቡድኖች ብዛት 5 ብቻ የነበረ ቢሆንም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እንዳስታወቀው 10 ሃገራት በውድድሩ ላይ እንደሚካፈሉ ከሴካፋ ማረጋገጫ ተልኳል፡፡ ሴካፋ የሃገራቱን ማንነት ይፋ ባለማድረጉ ፌዴሬሽኑ ስለተሳታፊዎቹ ሃገራ ማንነት ምንም አላለም፡፡
ሶከር ኢትዮጵያ ባጣራችው መሰረት ከኤርትራ ውጪ 10 የሴካፋ ሃገራት የሚሳተፉ ሲሆን የሱዳን ሁኔታ አጠራጣሪ በመሆኑ የተጋባዦች ብዛት 2 ይሆናል ተብሏል፡፡ እንደ ፌዴሬሽኑ ህዝብ ግንኙነት ገለፃም ሁለት ተጋባዥ ሃገራትን ጨምሮ በውድድሩ ላይ የሚካፈሉት ሃገራት 12 ሊደርሱ ይችላሉ ብለዋል፡፡
አቶ ወንድምኩን አያይዘውም ሴካፋን በተለያዩ ከተሞች ለማዘጋጀት ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ውድድሩን የሚያስተላልፈው ሱፐር ስፖርት እና ኢቢሲን አቀናጅቶ ውድድሩን በአዲስ አበባ ፣ ሃዋሳ እና ባህርዳር ላይ ለማዘጋጀት ውይይት እና ድርድር እያደረግን ነው፡፡ ውይይቱ ተጠናቆ ውሳኔ ላይ ሲደረስ የምናሳውቅ ይሆናል፡፡ ›› ብለዋል፡፡
ኬንያ ለሴካፋ ዝጅጅት ተጫዋቾችን ጠርታ ሀሙስ ዝግጅት የምትጀምር ሲሆን ታንዛንያ ፣ ዩጋንዳ ፣ ታንዛንያ እና ሩዋንዳም በዚህ ሳምንት የሴካፋ ዝግጅታቸውን እንደሚጀመሩ ታውቋል፡፡