የኢትዮጰያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን አፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ውጪ ሆኗል

የ2016 የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ በካሜሩን አስተናጋጅነት በመጪው ኦክቶበር 2016 ይካሄዳል፡፡ ካፍ ከኦክቶበር 21 እስከ 28 በካይሮ በተደረገው የካፍ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የማጣርያ ጨዋታዎቹን ድልድል ያወጣ ሲሆን የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን በማጣርያው ድልድል ላይ አልተካተተም፡፡

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የህዝብ ግንኙነት አቶ ወንድምኩን አላዩ በጉዳዩ ዙርያ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ በውድድሩ ላይ እንድትካፈል ይፋዊ ጥያቄ ለሃገራችን አልቀረበም፡፡

‹‹ ሃገራችን ከማጣያው ራሷን አላገለለችም፡፡ ከካፍ በማጣርያው እንድንካፈል ጥያቄ አልቀረበልንም አልያም ጥያቄ ቀርቦልን አልመለስንም፡፡ ስለዚህም ክፍተት ሊኖር ስለሚችል እያጣራን ነው፡፡ ከውድድሩ በስህተት ወጥተንም ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን በእጣ ማውጣት ስነ-ስርአቱ ላይ ተወካያችንን ልከን የነበረ በመሆኑ ስለ ጉዳዩ የሚያውቀው ነገር ካለ እንዲነግረን ጠርተነዋል፡፡ ›› ብለዋል፡፡

የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ በካፍ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ተካፍለው እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

በ2016 የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ማጣርያ 23 ሃገራት የሚሳተፉ ሲሆን በመጀመርያው ዙር 18 ሃገራት ከማርች 4 እስከ 6 / 2016 (የመጀመርያ) እና ከማርች 18-20/016 (የመልስ) እርስ በእርስ ይፋለማሉ፡፡ አሸናፊዎቹ 9 ሃገራት በቀጥታ ወደ ሁለተኛው ዙር ከሚያልፉ 5 ሃገራት ጋር በድጋሚ ከኤፕሪል 8-10/2016(የመጀመርያ) እና ከኤፕሪል 22-24/2016 (የመልስ) የደርሶ መልስ ፍልሚያ አድርገው የሚያፉት 7 ሃገራት ከአስተናጋጇ ካሜሩን ጋር በመሆን ኦክቶበር 2016 በካሜሩን ለሚደረገው የአፍሪካ ሴቶች ውድድር ያልፋሉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *