የወቅቱ የሊጉ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ አቤል ያለው ከኤምሬቱ ቡድን የዝውውር ጥያቄ ቀረበለት።

የሲዳማ ቡና እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አጥቂ አቤል ያለው ከተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች (UAE) ክለብ የዝውውር ጥያቄ እንደቀረበለት ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።
ሶከር ኢትዮጵያ ከተጫዋቹ ወኪል አዛሪያ ተስፋጽዮን እንዳገኘችው መረጃ ከሆነ በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ሁለተኛ ዲቪዚዮን የሚወዳደረውና ወደ ፕሮ ሊጉ ለማደግ ሰፊ እቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው አል ኢቲሃድ ስፖርት ክለብ (Al Ittihad Sports Club) ለአጥቂው ይፋዊ ጥያቄ አቅርቧል።
ክለቡ አቤል ያለው ዘንድሮ ባሳየው ጥሩ አቋም መነሻነት ለአንድ የውድድር ዓመት (ለ2026/27) የሚቆይ ውል ያቀረበ ሲሆን እንደ ተጫዋቹ ብቃት ክለቡ ውሉን ለተጨማሪ አንድ ዓመት የማራዘም መብት (Extension Option) ይኖረዋል።
አቤል ያለው ከሀገር ውጪ የመጫወት ዕድሉን ተጠቅሞ ወደ ኤምሬትስ ያመራል ወይስ በሀገር ውስጥ ይቆያል የሚለው ወደፊት የሚታወቅ ሲሆን ሶከር ኢትዮጵያ በተጫዋቹ በኩል የሚሰጡ ምላሾችን ይዛ የምትመለስ ይሆናል።

