ሪፖርት | ቢጫ ለባሾቹ የፍጻሜው ተፋላሚ መሆናቸውን አረጋግጠዋል

ሪፖርት | ቢጫ ለባሾቹ የፍጻሜው ተፋላሚ መሆናቸውን አረጋግጠዋል

ወልዋሎ ዓ/ዩዎች መቐለን በመለያ ምት በማሸነፍ የኢትዮጵያ ዋንጫ የፍጻሜ ተፋላሚ የሆኑበትን ትኬት ቆርጠዋል።

በሞቃታማ የአየር ሁኔታ ውስጥ በተጀመረው የኢትዮጵያ ዋንጫ ግማሽ ፍፃሜ ተጠባቂ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ መቐለ 70 እንደርታዎች ጥንቃቄን ቀዳሚ ምርጫቸው በማድረግ በቁጥር ወደ ኋላ አፈግፍገው ለመከላከል ጥረቶችን ሲያደርጉ በሌላ በኩል ወልዋሎ ዓ/ዩዎች በበኩላቸው በፈጣን መስመራቸው ታግዘው ግብ ለማግኘት ተጭነው ተጫውተዋል። በዚህም ዳዊት ገብሩ ያሻማለትን ኳስ ሰመረ ሀፍታይ ከመሬት ጋር አጋጭቶ መትቶት በግብ አግዳሚው የተመለሰበት አስቆጭ ሙከራ የወልዋሎዎችን የማጥቃት ፍላጎት ማሳያ ነበረች።

ጨዋታው በዚሁ ፍጥነት ሲቀጥል መቐለ 70 እንደርታዎችም ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል በመድረስ የአፀፋ ጥቃቶችን ሰንዝረዋል። በተለይም ስንታየሁ መንግስቱ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመምታት የወልዋሎውን ግብ ጠባቂ የፈተነበት ሙከራ እና በመቀጠል ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ ፍሬዘር ካሳ በግንባሩ ገጭቶት ለጥቂት በግቡ ቋሚ በኩል የወጣበት ኳስ መቐለዎችን መሪ ለማድረግ የተቃረቡ ድንቅ አጋጣሚዎች ነበሩ።

ከዕረፍት መልስ ወልዋሎዎች በተጫዋች ለውጥና በፈጣን ሽግግር ተጋጣሚያቸውን በተደጋጋሚ መፈተን ችለዋል። መቐለዎችም አልፎ አልፎ ወደ ግብ ክልል በመጠጋት ምላሽ ለመስጠት የሞከሩ ሲሆን በተለይም ፕሪንስ ኦፍሪ ከሳጥን ውጭ አክርሮ መትቶት ለጥቂት የወጣው ኳስ እጅግ አስቆጪ ነበር። ሆኖም መደበኛው የጨዋታ ሰዓት ያለ ምንም ግብ 0 ለ 0 በመጠናቀቁ አሸናፊውን ለመለየት ጨዋታው ወደ መለያ ምት አምርቷል።

ባለፉት መደበኛ ደቂቃዎች ግብ ሳይቆጠር ወደ መለያ ምት ያመራው ይህ ጨዋታ እጅግ ረጅም እና አስገራሚ ፉክክር ያስተናገደ እና በጭንቀት የታጀበ ነበር። ሁለቱም ቡድኖች እስከ 9 (በድምሩ 18 መለያ ምቶችን የመቱ ሲሆን በመጨረሻም ቢጫ ለባሾቹ ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲዎች መቐለ 70 እንደርታን 7-6 በማሸነፍ የኢትዮጵያ ዋንጫ የፍጻሜ ተፋላሚ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። ይህንን ተከትሎ ከኢትዮጵያ መድን እና ሲዳማ ቡና አሸናፊ ጋር የፍፃሜ ፍልሚያቸውን የሚያደርጉ ይሆናል።