ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ወልዋሎ ዓ/ዩ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

የወልዋሎ ዓ /ዩ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ የ13ኛ ሳምንት የነገ ጨዋታን የተመለከቱ ጉዳዮችን እንዲህ ተመልክተናቸዋል።

ዘጠነኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ወልዋሎ ዓ /ዩ ከመሪው ኢትዮጵያ ቡና በአንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ በሁለተኝነት የተቀመጠው ቅዱስ ጊዮርጊስን ነገ 09፡00 ላይ በትግራይ ስታድየም ያስተናግዳል። በሳምንቱ አጋማሽ አዳማ ላይ የ1-0 ሽንፈት የገጠማቸው ወልዋሎዎች ከሦስት የአቻ ውጤቶች በኋላ ያገኙትን የ11ኛ ሳምንት ድላቸውን ማስቀጠል ሳይችሉ ወጥ አቋም ማሳየት የተሳናቸው ቢሆንም በሊጉ ያለው የነጥብ መቀራረብ እና አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ያላቸው መሆኑ ሲታይ ያሉበትን ሁኔታ እምብዛም አስጊ አያደርገውም። በአንፃሩ አራት ተከታታይ ጨዋታዎችን በድል የተወጣው ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ጠንካራ አቋም ላይ ይገኛል። በነዚህ ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ የተቆጠረበት ቅዱስ ጊዮርጊስ ይህን ጨዋታ ማሸነፍ ከቻለ የኢትዮጵያ ቡና ውጤት እስኪታወቅ ድረስ ወደ አንደኝነት የመምጣት ዕድልም ይኖረዋል።

ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጉዳት ላይ የሚገኙት ዋለልኝ ገብሬ እና ኤፍሬም ኃይለማርያም አሁንም ያልተመለሱለት ሲሆን በአዳማው ጨዋታ የቀይ ካርድ ሰለባ የሆነው አፈወርቅ ኃይሉም ከነገው ጨዋታ ውጪ ሆኗል። ከዚህ በተጨማሪ ከጉዳት አገግሞ ላለፉት ሁለት ቀናት ልምምድ የሰራው ሬችሞንድ አዶንጎ የመሰለፍ ጉዳይም አጠራጣሪ ነው። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል መሀሪ መና እና አብዱልከሪም መሀመድ ጉዳት ላይ የሚገኙ ሲሆን በደደብቱ ጨዋታ ተጎድቶ የወጣው ሳላዲን በርጌቾ እና አሜ መሀመድም በነገው ጨዋታ አይኖሩም።

ሁለቱ ቡድኖች በጨዋታው ማጥቃትን መሰረት ያደረገ አቀራረብ እንደሚኖራቸው ይታመናል። በአዳማው ጨዋታ ያለተፈጥሯዊ አጥቂ ወደ ሜዳ የገቡት ወልዋሎዎች ከፊት ከነበረባቸው ድክመት አንፃር ምናልባትም የፊት አጥቂያቸው ኦዶንጎን ወደ ሜዳ ሊመልሱት እንደሚችሉ ይገመታል። ቡድኑ አማካይ ክፍል ላይ ኳስ በመያዝ የጊዮርጊስ የመስመር ተመላላሾች የማጥቃት ኃላፊነትን ተከትሎ ሊያገኝ በሚችለው ክፍተት በተለይም በኤፍራም አሻሞ በኩል አጋድሎ ሊያጠቃም ይችላል። በተቃራኒው የፊት መስመር አማራጮቹ የሰፉለት ቅዱስ ጊዮርጊስ የወልዋሎ የማጥቃት አቀራረብ ከተከላካዮች ጀርባ የሚተወውን ክፍተት በአቤል ያለው ፍጥነት ለመጠቀም የመሞከር ዕቅድ ሊኖረው ይችላል። ባለሜዳዎቹ ለግብ ክልላቸው ቀርበው በሚከላከሉባቸው ወቅቶች ግን ቅዱስ ጊዮርጊስ መሀል ለመሀል ከሚሰነዝረው ጥቃት ይልቅ በመስመር ተመላላሾቹ በኩል ወደ ውስጥ የሚጥላቸው ኳሶች የመበርከት ዕድል ይኖራቸውል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ወልዋሎ ዓ /ዩ ወደ ሊጉ በመጣበት የአምናው የውድድር ዓመት ከተገናኙባቸው ጨዋታዎች የመጀመሪያው ያለግብ ሲጠናቀቅ በሁለተኛው ቅዱስ ጊዮርጊስ 1-0 አሸንፏል።

– በትግራይ ስታደየም ስድስት ጨዋታዎች ያደረገው ወልዋሎ ግማሹን ሲያሸንፍ ሁለቴ ነጥብ ተጋርቶ አንድ ጊዜ ደግሞ ተሸንፏል። ቡድኑ ያሸነፋቸው ሦስት ጨዋታዎች በ1-0 ውጤት የተጠናቀቁ ነበሩ።

– አራት ጊዜ ከአዲስ አበባ ውጪ የተጫወቱት ቅዱስ ጊዮርጊሶች አንድ ጊዜ ሲሸነፉ አንድ ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ግን ወደ ሀዋሳ እና ድሬዳዋ ካደረጉት ጉዞ በ1-0 ድል ተመልሰዋል።

ዳኛ

– ጨዋታው በኄኖክ አክሊሉ የመሀል ዳኝነት የሚመራ ይሆናል። አርቢትሩ እስካሁን ሁለት ጨዋታዎችን የዳኘ ሲሆን አንድ የቢጫ እና ሁለት የቀይ ካርዶችን ሲመዝ ሁለት የፍፁም ቅጣት ምቶችንም ሰጥቷል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወልዋሎ ዓ.ዩ (4-3-3)

አብዱልዓዚዝ ኬይታ

እንየው ካሳሁን –  ደስታ ደሙ – ቢኒያም ሲራጅ – ብርሀኑ ቦጋለ

ብርሀኑ አሻሞ – አስራት መገርሳ – አማኑኤል ጎበና

ፕሪንስ ሰቨሪንሆ – ሪችሞንድ ኦዶንጎ – ኤፍሬም አሻሞ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (3-5-2)

ፓትሪክ ማታሲ

አስቻለው ታመነ  – ምንተስኖት አዳነ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ

በኃይሉ አሰፋ – ሙሉዓለም መስፍን – ናትናኤል ዘለቀ – ኄኖክ አዱኛ

ታደለ መንገሻ

ሳላሀዲን ሰዒድ – አቤል ያለው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *