ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ፋሲል ከነማ ከ አዳማ ከተማ

ከነገ የ13ኛ ሳምንት ጨዋታዎች መካከል ፋሲል ከነማ እና አዳማ ከተማን በሚያገናኘው ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።

በዚህ ሳምንት ከሚደረጉ ጠንካራ ጨዋታዎች መካከል አንዱ የሆነው የፋሲል እና አዳማ ፍልሚያ አፄ ፋሲለደስ ስታድየም ላይ በ09፡00 ይጀምራል። በሳምንቱ አሳዛኝ እና አነጋጋሪ በነበረው ክስተት ደጋፊዎቻቸውን በመኪና አደጋ ያጡት ፋሲሎች ከአማራ ደርቢ አንድ ነጥብ ይዘው መመለስ ችለው ነበር። አፄዎቹ በእስካሁኑ መልካም ጉዟቸው ከቀጠሉ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች እያሏቸው ከመሪው በአራት ነጥቦች ልዩነት የተቀመጡ በመሆኑ ወደ ሊጉ አናት የመድረስ ዕድላቸው በእጃቸው ይገኛል። በተመሳሳይ ጠንካራ አቋም ላይ የሚገኘው አዳማ ከተማም ቀስ በቀስ ደረጃውን አሻሽሎ ከነገ ተጋጣሚው ቀጥሎ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ከመጨረሻዎቹ አምስት ጨዋታዎቻቸው ሁለት ነጥቦች ብቻ የጣሉት አዳማዎች ወደ ዋንጫ ፉክክሩ በትክክል መምጣታቸውን ለማረጋገጥ ከጎንደር ይዘው የሚመጡት ውጤት እጅግ ወሳኝ ይሆናል። ቡድኖቹ የሚገኙበት ወቅታዊ አቋም ጥሩ መሆን ከዚህ በፊት ካላቸው ተመጣጣኝ የእርስ በርስ ግንኙነት ጋር ተዳምሮ ጨዋታውን ከፍ ያለ ግምት አሰጥቶታል።

በነገው ጨዋታ ሰባት የሚደርሱ የፋሲል ከነማ ተጫዋቾች ክለባቸውን ማገልገል አይችሉም። ከነዚህ ውስጥ ሙጂብ ቃሲም ፣ ያስር ሙገርዋ ፣ ኢዙ አዙካ ፣ ኤፍሬም አለሙ እና ፋሲል አስማማው ጉዳት ላይ የሚገኙ ሲሆን በዛብህ መለዮ እና ዮሴፍ ዳሙዬም በህመም ምክንያት ጨዋታው ያልፋቸዋል። አዳማ ከተማ በበኩሉ እጅግ ወሳኝ አማካዩ ከነዓን ማርክነህ ከጉዳት ሲመለስለት ኤፍሬም ዘካሪያስ ፣ ሰራፌል ጌታቸው እና አንዳርጋቸው ይላቅ በጉዳት ቡልቻ ሹራ ደግሞ በወልዋሎው ጨዋታ በተመለከተው የቀይ ካርድ በቅጣት የማይሰለፉ ይሆናል።

ባለሜዳዎቹ ፋሲል ከነማዎች የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን በመያዝ በአጫጭር ቅብብሎች ወደ አዳማ የግብ ክልል ለመግባት እንደሚጥሩ ይጠበቃል። በዚህ ሂደት ውስጥ በቡድኑ የመሀል እና የፊት መስመር ተሰላፊዎች መካከል የሚኖረው የቅብብል ስኬት ድንቅ አቋም ላይ ከሚገኘው የአዳማው ተከላካይ አማካይ ኢስማኤል ሳንጋሪ ፈተና እንደሚገጥመው ይታሰባል። ፋሲሎች በተሻለ ሁኔታ ክፍተቶችን ሊያገኙ የሚችሉትም በቀኝ እና በግራ አቅጣጫ ይየመሆን ዕድሉ የሰፋ ነው። ሆኖም የቡድኑ የጉዳት ዜና መበራከት ለአሰልጣኝ ውበቱ አባተ አማራጮችን ሊያሳንስ መቻሉ ለቡድኑ ዋናው የነገ ከባድ ፈተና ይሆናል። ከነዓን የተመለሰላቸው አዳማዎች የማጥቃት ሽግግሮቻቸው የተሻለ ፍጥነት እና ስኬት የማሳየት ዕድላቸው የሰፋ ነው። የዳዋ ሆቴሳ እና በረከት ደስታ ጥሩ አቋም ላይ መገኘት እንዲሁም የዐመለ ሚልኪያስ በወጥነት ወደ መጀመሪያ አሰላለፍ መምጣት በጥሩ ጎን የሚነሳ ቢሆንም ቡልቻ ሹራ አለመኖሩ ግን የቡድኑ ጥቃት በጣሙን ወደ በረከት አቅጣጫ ያደላ ተገማች እንዳይሆን ያሰጋዋል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ክለቦቹ እስካሁን በሊጉ በተገናኙባቸው አራት ጨዋታዎች ተመጣጣኝ ውጤት አላቸው ፤ ሁለት ጊዜ ነጥብ ሲጋሩ አንድ አንድ ጊዜ ደግሞ ተሸንፈዋል። በጨዋታዎቹ ሁለት ሁለት ጊዜ ኳስ እና መረብን አገናኝተዋል።

– ጎንደር ላይ ከተገናኙባቸው ሁለት ጨዋታዎች ውስጥ አንዱን ፋሲሎች ሲያሸንፉ ሌላኛው ያለግብ ተጠናቋል።

– እስካሁን ሜዳቸው ላይ ሽንፈት ያልገጠማቸው ፋሲል ከነማዎች ከአምስት ጨዋታዎች ሦስቱን ድል አድርገዋል ፤ ኢትዮጵያ ቡናን ካስተናገዱበት ጨዋታ ውጪም በሁሉም ላይ ግብ አስቆጥረዋል።

– አምስት ጊዜ ከሜዳቸው የወጡት አዳማዎች ሁለት ጊዜ በሽንፈት እና በአቻ ሲመለሱ አንድ ጊዜ ድል ቀንቷቸውል። አዳማዎች በመጨረሻዎቹ ሁለት የሜዳ ውጪ ጨዋታዎቻቸው አልተሸነፉም።

ዳኛ

– ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት ይመራዋል። አርቢትሩ እስካሁን በአራት ጨዋታዎች ላይ የዳኘ ሲሆን 19 የማስጠነቂያ እና አንድ የቀይ ካርዶችን መዟል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ፋሲል ከነማ (4-3-3)

ሚኬል ሳማኬ

ሰዒድ ሁሴን – ያሬድ ባየህ –  ከድር ኩሊባሊ – አምሳሉ ጥላሁን

ሰለሞን ሀብቴ – ሐብታሙ ተከስተ – ሱራፌል ዳኛቸው

ሽመክት ጉግሳ – ኤዲ ቤንጃሚን – አብዱራህማን ሙባረክ

አዳማ ከተማ (4-2-3-1)

ሮበርት ኦዶንካራ

ሱለይማን ሰሚድ – ምኞት ደበበ – ተስፋዬ በቀለ – ሱለይማን መሀመድ

አዲስ ህንፃ – ኢስማኤል ሳንጋሪ

ዐመለ ሚልኪያስ – ከነዓን ማርክነህ – በረከት ደስታ

ዳዋ ሆቴሳ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *